አስቴር ወደ ንጉሡ ዙፋን ትቀርባለች
አስቴር ንጉሣዊ ልብሷን ለብሳ ሳትጠራ በውስጠኛው አደባባይ ትቆማለች፤ የወርቁ በትር ይዘረጋላታል፤ የመንግሥቱም እኩሌታ ይቀርብላታል። እርስዋ የምትለምነው ግብዣን ብቻ ነው፤ ከዚያም ሁለተኛ። ሐማ ደስ ብሎት ይወጣል፤ በመርዶክዮስ ተቆጥቶ ግንድ ያሠራል።
5 1በሦስተኛው ቀን አስቴር የንግሥና ልብስ ለብሳ በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ አደባባይ ከንጉሡ አዳራሽ ፊት ለፊት ቆመች። ንጉሡም በአዳራሹ ውስጥ በንጉሣዊ ዙፋኑ ላይ ከቤተ መንግሥቱ መግቢያ ትይዩ ተቀምጦ ነበር። 2ንጉሡ ንግሥቲቱ አስቴርን በአደባባዩ ቆማ ባየ ጊዜ፣ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘች፤ በእጁም የያዘውን የወርቅ በትረ መንግሥት ዘረጋላት። አስቴርም ቀርባ የበትሩን ጫፍ ዳሰሰች።
3ንጉሡም፣ “ንግሥት አስቴር ሆይ፣ ምን ሆነሻል? የምትለምኚውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ ይሰጥሻል” አላት።
4አስቴርም፣ “ንጉሡ ቢወድ፣ እርሱና ሐማ ዛሬ ላዘጋጀሁት ግብዣ ይምጡ” አለች።
5ንጉሡም፣ “አስቴር እንዳለችው ይደረግ ዘንድ ሐማን ፈጥናችሁ አምጡ” አለ። ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።
6ንጉሡም የወይን ጠጅ ሲጠጡ፣ “አስቴር ሆይ፣ ልመናሽ ምንድን ነው? ይፈጸምልሻል። ጥያቄሽስ ምንድን ነው? የመንግሥቴ እኩሌታም ቢሆን፣ የአንቺ ነው” አላት።
7አስቴርም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ልመናዬና ጥያቄዬ ይህ ነው፦ 8በንጉሡ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ ንጉሡም ልመናዬን ሊሰጠኝና ጥያቄዬን ሊፈጽምልኝ ቢወድ፣ ንጉሡና ሐማ ለእነርሱ ወደማዘጋጀው ግብዣ ይምጡ። ነገም ንጉሡ እንዳለው አደርጋለሁ።”
የሐማ ቍጣ በመርዶክዮስ ላይ ይነሣል
9ሐማም በዚያ ቀን ደስ ብሎትና እየተደሰተ ወጣ። ነገር ግን መርዶክዮስ በንጉሡ በር ላይ ሳይነሣና በፊቱ ሳይንቀጠቀጥ ባየ ጊዜ፣ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተቈጣ። 10ነገር ግን ሐማ ራሱን ገትቶ ወደ ቤቱ ሄደ። ወዳጆቹንና ሚስቱን ዜሬሽን አስጠራ፤ 11ሐማም የሀብቱን ክብር፣ የብዙ ወንዶች ልጆቹን፣ ንጉሡም ከሹማምቱና ከአገልጋዮቹ በላይ ከፍ ከፍ አድርጎ እንዳከበረው ነገራቸው።
12ሐማም፣ “ይህ ብቻ አይደለም” ብሎ ጨመረ፤ “ንግሥት አስቴር ከንጉሡ ጋራ እኔን ብቻ ወደ ግብዣዋ ጠራች፤ ነገም ደግሞ ከንጉሡ ጋራ ተጠርቻለሁ። 13ነገር ግን አይሁዳዊውን መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ተቀምጦ ባየሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህ ሁሉ ምንም አይጠቅመኝም።”
14ሚስቱ ዜሬሽና ወዳጆቹ ሁሉ፣ “ቁመቱ ሰባ አምስት ጫማ የሆነ ግንድ ይሠራ፤ ጥዋትም መርዶክዮስ በእርሱ ላይ እንዲሰቀል ንጉሡን ለምን፤ ከዚያም ደስ ብሎህ ከንጉሡ ጋራ ወደ ግብዣው ሂድ” አሉት። ይህም ሐማን ደስ አሰኘው፤ ግንዱም እንዲሠራ አደረገ።