ንጉሡ መርዶክዮስን ያከብረዋል
ንጉሡ እንቅልፍ አጥቶ የታሪክ መዝገቡ እንዲነበብለት ያደርጋል፤ መርዶክዮስም ከቶ እንዳልተሸለመ ይረዳል። ሐማ መርዶክዮስ እንዲሰቀል ለመለመን ሲመጣ፣ አንድን ሰው እንዴት ማክበር እንደሚገባ ይጠየቃል — የራሱን ሕልም ይገልጻል፤ ከዚያም መርዶክዮስን በአደባባይ እየመራ ይህንኑ ማወጅ ይገደዳል። ቤተ ሰቡም ውድቀቱ እንደሚመጣ ያያሉ።
6 1በዚያች ሌሊት ንጉሡን እንቅልፍ ራቀው፤ የመታሰቢያ መጽሐፉ፣ ይኸውም የዜና መዋዕሉ፣ መጥቶ በፊቱ እንዲነበብ አዘዘ። 2መርዶክዮስ፣ ደጃፉን ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱን፣ ቢግታናንና ቴሬሽን፣ ንጉሥ ጠረክሲስን ሊገድሉ ስለ ፈለጉ እንደ ከሰሳቸው ተጽፎ ተገኘ። 3ንጉሡም፣ “መርዶክዮስ ስለዚህ ነገር ምን ክብርና ምን ታላቅነት ተሰጠው?” ብሎ ጠየቀ። የሚያገለግሉትም፣ “ምንም አልተደረገለትም” ብለው መለሱ።
4ንጉሡም፣ “በቅጥሩ ውስጥ ያለው ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ሐማም መርዶክዮስን ባዘጋጀው መሰቀያ ላይ እንዲሰቅለው ሊጠይቀው ወደ ቤተ መንግሥቱ ውጪኛ ቅጥር ገብቶ ነበር።
5የንጉሡ አገልጋዮችም፣ “እነሆ፣ ሐማ በቅጥሩ ውስጥ ቆሞአል” አሉት። ንጉሡም፣ “አስገቡት” አለ።
6ሐማም ገባ። ንጉሡም፣ “ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ምን ይደረግለት?” ብሎ ጠየቀ። ሐማም በልቡ፣ “ንጉሡ ከእኔ ይልቅ ማንን ሊያከብር ይወድዳል?” ብሎ አሰበ።
7ስለዚህ ሐማ ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው፣ 8ንጉሡ የለበሰውን የንግሥና ልብስ፣ ንጉሡ የተቀመጠበትን ፈረስ፣ በፈረሱም ራስ ላይ የንግሥና አክሊል ያምጡ። 9ልብሱንና ፈረሱን ከንጉሡ የተከበሩ መኳንንት ለአንዱ ይስጡት፤ ንጉሡ ሊያከብረው የሚወድደውን ሰው ያልብሱት፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጠው በከተማዪቱ አደባባይ ያዙሩት፤ በፊቱም፣ ‘ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል!’ ብለው ይጩኹ።”
10ንጉሡም ሐማን፣ “ፍጠን፤ እንዳልኸው ልብሱንና ፈረሱን ይዘህ፣ በንጉሡ በር ለተቀመጠው ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ እንዲሁ አድርግለት፤ ከተናገርኸውም ነገር ምንም አትተው” አለው።
11ሐማም ልብሱንና ፈረሱን ወስዶ መርዶክዮስን አለበሰው፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጦ በከተማዪቱ አደባባይ አዞረው፤ በፊቱም፣ “ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል” እያለ ጮኸ።
12ከዚያም በኋላ መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ፤ ሐማ ግን እያዘነ ራሱን ተከናንቦ ወደ ቤቱ ፈጥኖ ሄደ። 13ሐማም የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ለዜሬሽና ለወዳጆቹ ሁሉ ነገረ። አማካሪዎቹና ሚስቱ ዜሬሽም፣ “በፊቱ መውደቅ የጀመርኸው መርዶክዮስ አይሁዳዊ ስለሆነ፣ ልታሸንፈው አትችልም፤ በፊቱ በእርግጥ ትወድቃለህ” አሉት። 14ገና ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ሳሉ የንጉሡ ጃንደረቦች መጡ፤ ሐማንም አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ፈጥነው ወሰዱት።