ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ ወሬ ደረሰ
የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ፈርሰው ፍርስራሽ ሆነዋል፤ ነህምያም ሕዝቡን መልሰው እንዲሠሯቸው ይመራል። በማእከሉ ሕዝቡን በየምድረ በዳው ሁሉ የደገፈውን አብ የሚያስታውስ ታላቅ ጸሎት አለ።
1 1የአካልያ ልጅ የነህምያ ቃላት። በሃያኛው ዓመት፣ በኪስሌቭ ወር፣ በሱሳ ግንብ ውስጥ ነበርሁ፤ a a v1 ኪስሌቭ የዕብራውያን ዘመን አቈጣጠር ዘጠነኛ ወር ሲኾን፣ ከኅዳር መጨረሻ እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ ይውላል።
2ከወንድሞቼ አንዱ ሃናኒ ከይሁዳ ከመጡ ሰዎች ጋራ መጣ፤ ከምርኮ ስለ ተረፉት፣ ስለ ዳኑት አይሁድና ስለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኋቸው። 3እነርሱም፣ “በምርኮ ተወስደው ከቀሩት መካከል በዚያ በአውራጃው ያሉት በታላቅ መከራና ውርደት ውስጥ ናቸው፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈርሷል፣ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ።
4ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀመጥሁ፣ አለቀስሁም፤ ለብዙ ቀናት እያዘንሁ፣ በሰማይ ባለው አባታችን ፊት እጦምና እጸልይ ነበር። 5እንዲህም አልሁ፤ “እባክህ፣ በሰማይ ያለህ አባቴ፣ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፣ ለሚወዱህና ትእዛዛትህን ለሚጠብቁ ኪዳንንና ጽኑ ፍቅርን የምትጠብቅ፤ 6ይህን ጸሎት ለመስማት ጆሮህ ያድምጥ፣ ዐይኖችህም ይከፈቱ፤ እኔ ባሪያህ ስለ እስራኤል ስለ ባሪያዎችህ አኹን ቀንና ሌሊት በፊትህ የምጸልየውን ጸሎት እንድትሰማ፤ እኛ እስራኤላውያን በአንተ ላይ የበደልነውን ኀጢአት እናገራለሁ፤ እኔና የአባቴ ቤት ኀጢአትን ሠርተናል። 7እጅግ በድለንሃል፤ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝከውን ትእዛዛት፣ ሥርዐቶችና ፍርዶች አልጠበቅንም።
8ለባሪያህ ለሙሴ የተናገርከውን ቃል እባክህ አስብ፤ ‘ታማኞች ባትኾኑ፣ በሕዝቦች መካከል እበትናችኋለሁ፤ 9ነገር ግን ወደ እኔ ብትመለሱ፣ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁና ብታደርጓቸው፣ የተበተኑት ሰዎቻችሁ በሰማይ ዳርቻ ቢኾኑ እንኳ፣ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤ ስሜም እንዲኖር ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ’ የሚለውን።
10እነርሱም በታላቅ ኀይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። 11እባክህ፣ ጌታዬ አባቴ፣ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፣ ስምህን ለመፍራት ደስ የሚላቸውን የባሪያዎችህንም ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬ ባሪያህን አሳካለት፣ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው።” በዚያን ጊዜ የንጉሡ የጽዋ አቀባይ ነበርሁ።