እርሱን ማግኘት ብችል ኖሮ
ኢዮብ ጠብ ሳይሆን ፍርድ ቤት ይፈልጋል። እግዚአብሔር የሚኖርበትን ቢያገኝ ጉዳዩን አቅርቦ ነጻ ይወጣ ነበር። እግዚአብሔር ግን በምሥራቅም በምዕራብም የለም፤ የወደደውንም ያደርጋል። ኢዮብ እንደ ወርቅ ሆኜ እወጣለሁ ይላል፤ ሆኖም በፍርሃት እንደ ተሸበረ ይቀራል።
23 1ኢዮብም መልሶ እንዲህ አለ፤ 2“ዛሬም ቢሆን ማማረሬ መራራ ነው፤ እያቃሰትሁም እጁ ከብዶብኛል። 3የት እንዳገኘው ባውቅ ኖሮ፣ ወደ መኖሪያውም በመጣሁ ነበር! 4ነገሬን በፊቱ ባቀረብሁ፣ አፌንም በመከራከሪያ በሞላሁ ነበር። 5የሚመልስልኝን ቃላት በተማርሁ፣ የሚነግረኝንም በተረዳሁ ነበር። 6በታላቅ ኀይሉ ይከራከረኝ ይሆንን? አይደለም፤ በርግጥ ያዳምጠኝ ነበር። 7በዚያ ቅን ሰው ከእርሱ ጋራ ይከራከር ነበር፤ በፈራጄም ለዘላለም ነጻ በወጣሁ ነበር። 8ነገር ግን ወደ ምሥራቅ ብሄድ፣ በዚያ የለም፤ ወደ ምዕራብም ብሄድ አላገኘውም። 9በሰሜን ሲሠራ አላየውም፤ ወደ ደቡብ ሲመለስ አላገኘውም። 10እርሱ ግን የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤ በፈተነኝም ጊዜ እንደ ወርቅ ሆኜ እወጣለሁ። 11እግሬ ፈለጉን አጥብቆ ተከትሏል፤ መንገዱን ጠብቄ ፈቀቅ አላልሁም። 12ከከንፈሮቹ ትእዛዝ ፈቀቅ አላልሁም፤ የአፉን ቃላት ከዕለት እንጀራዬ አብልጬ አከብራለሁ። 13እርሱ ግን አይለወጥም፤ ማንስ ሊመልሰው ይችላል? የሚፈልገውን ሁሉ ያደርጋል። 14ለእኔ የወሰነውን ይፈጽማልና፤ እንደዚህ ያለ ብዙ ነገርም በልቡ አለ። 15ስለዚህ በፊቱ እደነግጣለሁ፤ ባሰብሁትም ጊዜ እርሱን እፈራለሁ። 16እግዚአብሔር ልቤን አስደክሞታል፤ ሁሉን ቻዩም አስደንግጦኛል። 17ይሁንና በጨለማ ዝም አልተባልሁም፤ ፊቴን በሚሸፍነው ጥቅጥቅ ጨለማም ዝም አልተባልሁም።”