ያንብቡ። ይቀበሉ። ይጠቁሙ።

♥ አስተያየቶች

2 ነገሥት 19

መጽሐፍ

አባታችን ለሕዝቅያስ ጭንቀት ምላሽ ይሰጣል

ሕዝቅያስ የዛቻውን ደብዳቤ ወደ አብ ቤት ይዞ ገብቶ በፊቱ ይዘረጋዋል። ኢሳይያስም የእስራኤል ቅዱስ ፌዙን እንደ ሰማና ሰናክሬምን በመንጠቆና በልጓም ወደ አገሩ እንደሚመልሰው ይመልሳል። በዚያች ሌሊት ሰፈሩ ይመታል፤ ሰናክሬምም በአገሩ ይሞታል።

ምዕራፍ 19።

ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ አባታችን ቤት ገባ። የቤተ መንግሥት አዛዡን ኤልያቄምን፣ ጸሐፊውን ሳምናስንና ታላላቆቹን ካህናት ሁሉ ማቅ አልብሶ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ላካቸው። እንዲህም አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ዛሬ የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ልጆች ሊወለዱ ደርሰዋል፤ ነገር ግን ለመውለድ ኀይል የለም። ምናልባት ጌታው የአሦር ንጉሥ ሕያውን አባት ለመዘለፍ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል ሁሉ አባትህ ይሰማ ይሆናል፤ የሰማቸውንም ቃላት ይኰንናል። ስለዚህ በሕይወት ስለሚቀረው ቀሪ ሕዝብ ጸልይ።”

የንጉሥ ሕዝቅያስ ሎሌዎች ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፣

ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ አባታችን እንዲህ ይላል፤ የአሦር ንጉሥ ሎሌዎች የተሳደቡብኝን፣ የሰማሃቸውን ቃላት አትፍራ። በእርሱ ላይ መንፈስ አኖርበታለሁ፤ ወሬ ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በዚያም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ።”

የጦር አዛዡ የአሦር ንጉሥ ከለኪሶ መውጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ተመልሶ የአሦርን ንጉሥ ልብናን ሲወጋ አገኘው። ንጉሡም ስለ ኢትዮጵያ ንጉሥ ስለ ቲርሐቃ፣ “እነሆ፣ ሊወጋህ ተነሥቷል” የሚል ወሬ ሰማ። ስለዚህ እንደ ገና ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፤ “የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤ የምትታመንበት አምላክህ፣ ኢየሩሳሌም ለአሦር ንጉሥ እንደማትሰጥ ቃል በመግባት አያታልልህ። እነሆ፣ የአሦር ነገሥታት በየአገሩ ሁሉ ያደረጉትን፣ ፈጽመውም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ ታዲያ አንተ ትድናለህን? አባቶቼ ያጠፏቸውን አሕዛብ፣ ማለትም ጎዛንን፣ ካራንን፣ ሬጸፍን፣ በቴልሳር የነበሩትን የኤደንን ሰዎች አማልክቶቻቸው አድኗቸዋልን? የሐማት ንጉሥ፣ የአርጶድ ንጉሥ፣ የሲፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄናና የኢዋ ነገሥታት ወዴት አሉ?”

ሕዝቅያስ በአብ ፊት ዘረጋው

ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ እጅ ተቀብሎ አነበበው። ከዚያም ወደ አባታችን ቤት ወጥቶ በፊቱ ዘረጋው። ሕዝቅያስም በአባታችን ፊት እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “በኪሩቤል ላይ የተቀመጥህ የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን አንተ ፈጠርህ። አባታችን ሆይ፣ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይኖችህንም ገልጠህ እይ። ሕያውን አባት ለመዘለፍ የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ። አባታችን ሆይ፣ በእውነት የአሦር ነገሥታት አሕዛብንና አገሮቻቸውን አጥፍተዋል፤ አማልክቶቻቸውንም በእሳት ጥለዋል፤ እነርሱ አማልክት አልነበሩምና፤ ነገር ግን የሰው እጅ ሥራ፣ እንጨትና ድንጋይ ነበሩ። ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። አሁንም አባታችን ሆይ፣ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ አምላክ እንደ ሆንህ እንዲያውቁ ከእጁ አድነን።”

አባታችን የሰናክሬምን ትዕቢት ያዋርዳል

የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስም ወደ ሕዝቅያስ ልኮ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ አባታችን እንዲህ ይላል፤ ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ የጸለይከውን ጸሎት ሰምቻለሁ። አባታችን በእርሱ ላይ እንዲህ ይላል፤ ድንግሊቱ የጽዮን ሴት ልጅ ትንቅሃለች፤ ታፌዝብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ በኋላህ ራስዋን ትነቀንቃለች። ማንን ዘለፍህ፤ ማንንስ ሰደብህ? በማን ላይ ድምፅህን ከፍ አደረግህ፤ ዐይኖችህንም በትዕቢት አነሣህ? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው! በመልእክተኞችህ ጌታ አባትን ዘለፍህ፤ እንዲህም አልህ፤ በብዙ ሠረገሎቼ ወጥቻለሁ ወደ ተራሮች ከፍታ፣ ወደ ሊባኖስ ዳርቻ። ረጃጅሞቹን ዝግባዎቿን፣ የተመረጡ ጥዶቿን ቈረጥኩ። እጅግ ወደ ራቀው ከፍታዋ፣ ወደ ጥቅጥቅ ደኗ ደረስሁ። ጕድጓዶችን ቈፍሬ የባዕድን ውሃ ጠጣሁ፤ በእግሬ ጫማም የግብፅን ወንዞች ሁሉ አደረቅሁ። አልሰማህምን? ይህን ከረጅም ዘመን በፊት አደረግሁት፤ ከጥንት ዘመንም ጀምሬ አቀድኩት። አሁንም አንተ የተመሸጉ ከተሞችን የፍርስራሽ ክምር ታደርግ ዘንድ ፈጽሜዋለሁ። ነዋሪዎቻቸው ኀይላቸው አንሶ ደነገጡ፤ ዐፈሩም። እንደ ሜዳ ቡቃያ፣ እንደ ለጋ አረንጓዴ ቡቃያ፣ በጣራ ላይ እንደሚበቅል ሣር፣ ሳያድግ እንደሚጠወልግ ሆኑ። ነገር ግን መቀመጥህን፣ መውጣትህንና መግባትህን፣ በእኔ ላይ መቈጣትህንም ዐውቃለሁ። በእኔ ላይ ስለ መቈጣትህና ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ ትዕቢትህ፣ ቀለበቴን በአፍንጫህ፣ ልጓሜንም በከናፍርህ አኖራለሁ፤ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ።

ሕዝቅያስ ሆይ፣ ይህ ምልክትህ ነው፤ በዚህ ዓመት ከራሱ የበቀለውን ብሉ፤ በሚቀጥለው ዓመት ከዚያው የሚበቅለውን ብሉ፤ በሦስተኛው ዓመትም ዝሩ፤ አጭዱ፤ የወይን አትክልት ተክላችሁም ፍሬውን ብሉ። ከይሁዳ ቤት የተረፈው ዳግመኛ ከታች ሥር ይሰድዳል፤ ከላይም ፍሬ ያፈራል። ከኢየሩሳሌም ቀሪ ሕዝብ፣ ከጽዮን ተራራም የተረፉት ጭፍራ ይወጣሉና። የሰማይ ሠራዊት አባት ቅንዓት ይህን ያደርጋል።

“ስለዚህ አባታችን ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ ወደዚህች ከተማ አይገባም፤ በዚህም ፍላጻ አይወረውርም፤ በጋሻም ወደ ፊትዋ አይመጣም፤ በእርስዋም ላይ የከበባ ትል አይሠራም። በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤ ወደዚህች ከተማም አይገባም ይላል አባታችን። ይህችን ከተማ ስለ ራሴ ስልና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል እከላከላታለሁ፤ አድናታለሁም።”

በዚያችም ሌሊት የአባታችን መልአክ ወጥቶ በአሦር ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን መታ። በማለዳም ሰዎች ሲነሡ፣ ሁሉም ሬሳ ሆነው ተገኙ። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ሰፈሩን አንሥቶ ተመለሰ፤ ወደ ነነዌም ተመልሶ በዚያ ተቀመጠ። በአምላኩ በነሶሮክ ቤተ መቅደስ ሲሰግድ ሳለ፣ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ሸሹ። ልጁ አስራዶንም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

A young man reading the Father's Heart Bible (FHB) print edition in a coffee shop አሁን በኅትመት ይገኛል

አስተያየቶች

ሐሳብ፣ ጥያቄ፣ ወይም ይህ ምዕራፍ በልብዎ ያነሣሣው ቃል — እዚህ ያካፍሉ። እያንዳንዱ አስተያየት ስምዎን በአስተዋጽኦ አበርካቾች ግድግዳ ላይ ያሰፍራል።

ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ መቅዳትና ማጋራት ለሁሉም ክፍት ነው — መለያ አያስፈልግም። አስተያየት መስጠት፣ ቁጥሮችን ማድመቅና የደረሱበትን ቦታ ምልክት ማድረግ ከነጻ መለያ ጋራ ይመጣሉ፤ እያንዳንዱ አስተያየትም ስምዎን በአስተዋጽኦ አበርካቾች ግድግዳ ላይ ያሰፍራል።

ቤተሰቡን ይቀላቀሉ — በነጻ ነው →
  • እስካሁን ምንም አስተያየት የለም። ድምፅዎን በማሰማት የመጀመሪያው ይሁኑ።