አባታችን ሕዝቅያስን ሰምቶ ፈወሰው
ቤቱን እንዲያስተካክል የተነገረው ሕዝቅያስ ፊቱን ወደ ግድግዳ መልሶ እንዴት እንደ ተመላለሰ እንዲያስብለት አብን ይለምናል። ዐሥራ አምስት ዓመት ይጨመርለታል፤ ለምልክትም ጥላው ወደ ኋላ ይመለሳል። ከዚያም ለባቢሎን መልእክተኞች ያለውን ሀብት ሁሉ ያሳያቸዋል፤ ሁሉም ወደዚያ እንደሚወሰድ ይሰማል።
20 1በዚያ ዘመን ሕዝቅያስ ታሞ ለሞት ተቃረበ። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም መጥቶ እንዲህ አለው፤ “አባታችን እንዲህ ይላል፤ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርም፤ ስለዚህ ቤትህን አደላድል።”
2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው አዙሮ ወደ አባታችን ጸለየ፤ 3“አባት ሆይ፤ በፊትህ በታማኝነት፣ በፍጹም ልብ እንደ ተመላለስኩ፣ በዐይንህም ፊት መልካም የሆነውን እንዳደረግሁ አስብ።” ሕዝቅያስም ምርር ብሎ አለቀሰ።
4ኢሳይያስም ገና ከመካከለኛው አደባባይ ሳይወጣ፣ የአባታችን ቃል እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ፤
5“ተመለስና የሕዝቤን መሪ ሕዝቅያስን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ የአባትህ የዳዊት አምላክ አባትህ እንዲህ ይላል፤ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ። እፈውስሃለሁ፤ በሦስተኛው ቀን ወደ ቤቴ ትወጣለህ። 6በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንም ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ አድናለሁ፤ ስለ ራሴና ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊት ስል ይህችን ከተማ እጠብቃለሁ።”
7ኢሳይያስም፣ “የበለስ ጥፍጥፍ አምጡ” አለ። አምጥተውም በእባጩ ላይ አደረጉት፤ እርሱም ዳነ።
8ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፣ “አባታችን እንደሚፈውሰኝ፣ በሦስተኛውም ቀን ወደ አባታችን ቤት እንደምወጣ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው።
9ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “አባታችን የገባውን ቃል እንደሚፈጽም ከአባታችን የሚሆንልህ ምልክት ይህ ነው፤ ጥላው ዐሥር ርምጃ ወደ ፊት ይሂድ ወይስ ዐሥር ርምጃ ወደ ኋላ ይመለስ?”
10ሕዝቅያስም፣ “ጥላው ዐሥር ርምጃ መርዘሙ ቀላል ነው፤ አይደለም፣ ዐሥር ርምጃ ወደ ኋላ ይመለስ” ብሎ መለሰ።
11ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ አባታችን ጮኸ፤ አባታችንም ጥላውን በአካዝ ደረጃ ላይ ወርዶ የነበረውን ዐሥር ርምጃ ወደ ኋላ መለሰው።
ሕዝቅያስ የባቢሎንን መልእክተኞች ተቀበለ
12በዚያ ጊዜ የባላዳን ልጅ የባቢሎን ንጉሥ ብሮዳክ ባላዳን ሕዝቅያስ ታሞ እንደ ነበር ሰምቶ ደብዳቤዎችንና ገጸ በረከትን ላከለት። 13ሕዝቅያስም ተቀብሎ የመዝገብ ቤቱን ሁሉ አሳያቸው፤ ብሩን፣ ወርቁን፣ ሽቱውን፣ መልካሙን ዘይት፣ የጦር መሣሪያ ቤቱን ሁሉ፣ በመጋዘኖቹም ውስጥ ያለውን ሁሉ አሳያቸው። ሕዝቅያስ በቤተ መንግሥቱም ሆነ በግዛቱ ሁሉ ያላሳያቸው ምንም ነገር አልነበረም።
14ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ፣ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡ?” ብሎ ጠየቀ። ሕዝቅያስም፣ “ከሩቅ አገር ከባቢሎን መጡ” አለ።
15“በቤተ መንግሥትህ ያዩት ምንድን ነው?” ብሎ ኢሳይያስ ጠየቀ። ሕዝቅያስም፣ “በቤተ መንግሥቴ ያለውን ሁሉ አዩ” ብሎ መለሰ። “ከመዝገቦቼ መካከል ያላሳየኋቸው ምንም የለም።”
16ኢሳይያስም ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “የአባታችንን ቃል ስማ፤
17በቤተ መንግሥትህ ያለው ሁሉ፣ አባቶችህ እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚወሰድበት ዘመን ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፣ ይላል አባታችን። 18ከገዛ ልጆችህም፣ ከዘርህ የተወሰኑት ተወስደው በባቢሎን ንጉሥ ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ሆነው ያገለግላሉ።”
19ሕዝቅያስም፣ “የተናገርከው የአባታችን ቃል መልካም ነው” አለ፤ “በዘመኔ ሰላምና ጸጥታ አይኖርምን?” ብሎ አስቦ ነበርና።
20የሕዝቅያስ የቀሩት ሥራዎች፣ ኀይሉ ሁሉ፣ ውሃንም ወደ ከተማዪቱ ለማስገባት ኵሬውንና መስኖውን እንዴት እንደ ሠራ በይሁዳ ነገሥታት ዜና መዋዕል አልተጻፈምን? 21ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ ምናሴም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።