ምናሴ ይሁዳን ከአብ አራቀ
ምናሴ ሁሉን ያፈርሳል፤ የኮረብታ መስገጃዎችን መልሶ ይሠራል፣ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሰማይ ሠራዊት መሠዊያዎችን ያቆማል፣ የገዛ ልጁን በእሳት ያቃጥላል፣ መናፍስት ጠሪዎችን ይጠይቃል፣ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ይሞላል። አብ ከተማዪቱን ሰው ሳሕንን እንደሚወለውል እንደሚወለውላት ይናገራል። አሞን የአባቱን መንገድ ይቀጥላል፤ በቤተ መንግሥቱም ይገደላል።
21 1ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ። የእናቱ ስም ሔፍጺባ ነበር። 2ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ያስወጣቸውን የአሕዛብን አስጸያፊ ድርጊቶች በመከተል፣ በአባታችን ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 3አባቱ ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታ ላይ መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣልም መሠዊያዎች ሠራ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው የአሼራን ዐምድ አቆመ፤ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፤ አገለገላቸውም።
4በአባታችን ቤት ውስጥም መሠዊያዎች ሠራ፤ አባታችን ስለዚህ ቤት፣ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ” ብሎ ነበር።
5በአባታችንም ቤት በሁለቱም አደባባዮች ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎች ሠራ። 6የገዛ ልጁን በእሳት ሠዋ፤ ጥንቆላንና ሟርትን ተለማመደ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና አስማተኞችንም አማከረ። በአባታችን ፊት እጅግ ብዙ ክፉ ነገር በማድረግ አስቈጣው።
7የሠራውን የተቀረጸ የአሼራ ምስል አባታችን ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን ስለ ተናገረለት ቤት ውስጥ አቆመ፤ አባታችንም እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኋት በዚህ ቤትና በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ። 8ያዘዝኋቸውን ሁሉ በጥንቃቄ ቢጠብቁ፣ ባሪያዬ ሙሴ የሰጣቸውንም ሕግ ሁሉ ቢፈጽሙ፣ የእስራኤልን እግር ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር ዳግመኛ አላንከራትትም።”
9እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ምናሴም አባታችን ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ ይልቅ የባሰ ክፉ ነገር እንዲያደርጉ አሳታቸው።
10ስለዚህ አባታችን በባሪያዎቹ በነቢያት እንዲህ ተናገረ፦
11“የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን አስጸያፊ ነገር ስላደረገ፣ ከእርሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን ሁሉ ይልቅ የከፋ ነገር ስለ ሠራ፣ በጣዖታቱም ይሁዳን ስላስኀጢአ፣ 12ስለዚህ የእስራኤል አምላክ አባታችን እንዲህ ይላል፦ የሚሰማው ሁሉ ሁለቱም ጆሮዎቹ የሚያቃጭሉበትን መዓት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።
13“በኢየሩሳሌም ላይ የሰማርያን መለኪያ ገመድና የአክዓብን ቤት የሚዛን ገመድ እዘረጋለሁ፤ ሰው ሳሕንን እንደሚያብስ፣ አብሶም እንደሚገለብጥ ኢየሩሳሌምን አብሳታለሁ፤ እገለብጣታለሁም። 14ከርስቴም የቀረውን እተዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ዘረፋና ምርኮ ይሆናሉ፤ 15ይህም አባቶቻቸው ከግብፅ ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ነገር ስላደረጉና ስላስቈጡኝ ነው።”
16ከዚህም በላይ ምናሴ ይሁዳን ወዳስኀጢአው ኀጢአት ሳይቈጠር፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላ ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ፤ በአባታችንም ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
17የቀረው የምናሴ ታሪክ፣ ያደረገው ሁሉ፣ የሠራውም ኀጢአት በይሁዳ ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎ የለምን? 18ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱ አትክልት ስፍራ፣ በዑዛ አትክልት ተቀበረ። በእርሱም ፋንታ ልጁ አሞጽ ነገሠ።
አሞጽ ነገሠ፤ አብንም ተወ
19አሞጽ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ። የእናቱ ስም ምሱሌሜት ይባል ነበር፤ እርሷም ከዮጥባ የመጣችው የኀሩጽ ልጅ ነበረች። 20አባቱ ምናሴ እንዳደረገው፣ በአባታችን ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 21በአባቱ መንገድ ሁሉ ተመላለሰ፤ አባቱ ያገለገላቸውን ጣዖታት አገለገለ፤ ሰገደላቸውም። 22የአባቶቹን አምላክ አባታችንን ተወ፤ በአባታችንም መንገድ አልተመላለሰም። 23የአሞጽም ሹማምንት በእርሱ ላይ አሢረው በገዛ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ንጉሡን ገደሉት። 24የምድሪቱ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሢሩበትን ሁሉ ገደሉ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁን ዮስያስን አነገሡ። 25የቀረው የአሞጽ ታሪክ በይሁዳ ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎ የለምን? 26በዑዛ አትክልት ስፍራ ባለው መቃብሩ ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ዮስያስ ነገሠ።