ገና በአብ ውስጥ እያደግን
የቆሮንቶስ ሰዎች ወደ ደጋፊ ቡድኖች እየተከፋፈሉ ነው፤ አንዱ እኔ የጳውሎስ ነኝ፣ ሌላው እኔ የአጵሎስ ነኝ ይላል። ጳውሎስም ይህን ሕፃንነት ይለዋል። የሚተክልም የሚያጠጣም ምንም አይደሉም፤ የሚያሳድገው አብ ነው። እያንዳንዱ በአንዱ መሠረት ላይ የሚገነባው በእሳት ይገለጣል።
3 1ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፤ እንደ መንፈሳውያን ልናገራችሁ አልቻልኩም፤ ነገር ግን እንደ ሥጋውያን፣ በክርስቶስም እንደ ሕፃናት ተናገርኋችሁ። 2ገና ዝግጁ ስላልነበራችሁ፣ ጠንካራ ምግብ ሳይሆን ወተት ሰጠኋችሁ። አሁንም ቢሆን ገና ዝግጁ አይደላችሁም። 3ገና ሥጋውያን ናችሁ። ቅናትና ክርክር በመካከላችሁ ስላለ፣ ሥጋውያን ሆናችሁ በሰው ልማድ የምትኖሩ አይደላችሁምን? 4አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣” ሌላውም፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ፣” ሲል፣ እንደ ተራ ሰዎች የምትሆኑ አይደላችሁምን?
5እንግዲህ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ ለእያንዳንዳቸው እንደ ሰጣቸው፣ በእነርሱ በኩል ያመናችሁባቸው አገልጋዮች ናቸው። 6እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ ነገር ግን ያሳደገው አባታችን ነው። 7ስለዚህ የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው ምንም አይደለም፤ ዋናው የሚያሳድገው አባታችን ነው። 8የሚተክለውና የሚያጠጣው አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ራሱ ድካም የራሱን ዋጋ ይቀበላል። 9እኛ የአባታችን አብረው ሠራተኞች ነንና፤ እናንተም የእርሱ እርሻ፣ የእርሱ ሕንፃ ናችሁ።
10አባታችን በሰጠኝ ጸጋ መሠረት፣ እንደ ጥበበኛ ዋና ግንበኛ መሠረት ጣልሁ፤ ሌላውም በእርሱ ላይ ይገነባል። እያንዳንዱ በእርሱ ላይ እንዴት እንደሚገነባ ይጠንቀቅ። 11ከተጣለው መሠረት በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊጥል አይችልምና፤ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 12ማንም በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮች፣ በእንጨት፣ በሣር ወይም በገለባ ቢገነባ፣ 13የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ ቀኑ ይገልጠዋልና፤ እሳት ይፋ ያደርገዋልና፤ ያም እሳት የእያንዳንዱ ሥራ ምን እንደ ሆነ ይፈትነዋል። 14ማንም የገነባው ሥራ ጸንቶ ቢቆም፣ ዋጋ ይቀበላል። 15የማንም ሥራ ቢቃጠል፣ ጉዳት ይደርስበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፣ ነገር ግን በእሳት ውስጥ እንደ ማለፍ ያህል ብቻ ነው።
16የአባታችን ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ፣ የአባታችንም መንፈስ በእናንተ ውስጥ እንደሚኖር አታውቁምን? 17ማንም የአባታችንን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ፣ አባታችን እርሱን ያፈርሰዋል። የአባታችን ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ያም ቤተ መቅደስ እናንተ ናችሁ።
18ማንም ራሱን አያታልል። ከእናንተ መካከል ማንም በዚህ ዘመን ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፣ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። 19የዚህ ዓለም ጥበብ በአባታችን ዘንድ ሞኝነት ነውና። መጽሐፍ፣ “ጥበበኞችን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፣” ይላልና፤ 20ደግሞም፣ “አባታችን የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል፣” ይላል። 21ስለዚህ ማንም በሰዎች አይመካ። ሁሉ ነገር የእናንተ ነውና፤ 22ጳውሎስ ቢሆን፣ አጵሎስ ቢሆን፣ ኬፋ ቢሆን፣ ዓለም ቢሆን፣ ሕይወት ቢሆን፣ ሞት ቢሆን፣ የአሁኑ ቢሆን፣ የሚመጣው ቢሆን ሁሉ የእናንተ ነው፤ 23እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የአባታችን ነው።