ቤተ መቅደሱ አይቆምም
ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ ሲነገራቸው ደቀ መዛሙርቱ መቼ እንደሆነ ይጠይቃሉ። ኢየሱስ ጦርነቶችን፣ ክህደትን፣ ሐሰተኛ መሲሖችን፣ የቀዘቀዘ ፍቅርን፣ ማንም ልብሱን ለመውሰድ የማይቆምበትን አስቸኳይ ሽሽት ይገልጻል። ያችን ቀን ግን ማንም አያውቅም — መላእክት አይደሉም፣ ወልድም አይደለም፣ አብ ብቻ እንጂ።
24 1ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ሲሄድ፣ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻዎች ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ።
2እርሱም መልሶ፣ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን?” አላቸው። “እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ እዚህ አይቀርም፤ ሁሉም ይፈርሳል።”
3ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ይህ መቼ እንደሚሆን፣ የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱም ምን እንደ ሆነ ንገረን” አሉት።
4ኢየሱስም መልሶ፣ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
5“ብዙዎች፣ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። 6ስለ ጦርነትና ስለ ጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አትደንግጡ። ይህ ሊሆን ግድ ነው፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። 7ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በልዩ ልዩ ስፍራም ራብና የምድር መናወጥ ይሆናል። 8ይህ ሁሉ ግን የምጥ ጣር መጀመሪያ ነው።
9በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 10በዚያን ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ፤ 11ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያስታሉ። 12ዐመፅም ስለሚበዛ፣ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፤ 13እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 14ይህም የመንግሥቱ ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም በኋላ መጨረሻው ይመጣል።
15ስለዚህ ነቢዩ ዳንኤል የተናገረው የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ አንባቢው ያስተውል፤ 16በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራሮች ይሽሹ።
17“በሰገነት ላይ ያለ ከቤቱ ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፤ 18በዕርሻም ያለ ልብሱን ሊወስድ ወደ ኋላ አይመለስ። 19በዚያ ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ሴቶች እንዴት የሚያስፈራ ይሆናል! 20ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ። 21በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ፣ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። 22እነዚያ ቀናት ባያጥሩ ኖሮ፣ ማንም ባልዳነ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ተመረጡት ሲባል እነዚያ ቀናት ያጥራሉ።
23በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፣ ክርስቶስ እዚህ አለ’ ወይም ‘እነሆ፣ እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ። 24ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችንና ድንቆችን ያደርጋሉ። 25እነሆ፣ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ።
26ስለዚህ፣ ‘እነሆ፣ በምድረ በዳ አለ’ ቢሏችሁ አትውጡ፤ ‘እነሆ፣ በእልፍኝ ውስጥ አለ’ ቢሏችሁ አትመኑ። 27መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ ድረስ እንደሚታይ፣ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። 28በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ፣ አሞራዎች በዚያ ይሰበሰባሉ።
29ከዚያ ወራት መከራ በኋላ ወዲያው፣ ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይም ኀይላት ይናወጣሉ። 30በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ የምድርም ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ የሰው ልጅም በኀይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል። 31መላእክቱንም በታላቅ የመለከት ድምፅ ይልካል፤ የተመረጡትንም ከአራቱ ነፋሳት፣ ከሰማይ ዳር እስከ ዳር ይሰበስቧቸዋል።
32ይህን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለሰልስ ቅጠልም ሲያወጣ፣ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። 33እንዲሁም ይህን ሁሉ ስታዩ፣ በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ። 34እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ፣ ይህ ትውልድ ከቶ አያልፍም። 35ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሎቼ ግን ከቶ አያልፉም።
አብ ብቻ ያውቃል
36“ያን ቀንና ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም፤ አብ ብቻ ያውቃል። 37እንደ ኖኅ ዘመን፣ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል። 38የጥፋት ውሃ ከመምጣቱ በፊት በነበሩት ቀናት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይድሩ ነበርና፤ 39የጥፋት ውሃም መጥቶ ሁሉንም እስኪወስድ ድረስ ምንም አላወቁም ነበር። የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል። 40በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፣ ሌላውም ይቀራል። 41ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋም ትቀራለች። 42እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ትጉ። 43ይህን ግን ዕወቁ፤ ባለቤቱ ሌባው በየትኛው የሌሊት ክፍል እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ ነበር፤ ቤቱም እንዲቈፈር ባልተወ ነበር። 44ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና።
45እንግዲህ ጌታው በጊዜው ምግባቸውን ይሰጣቸው ዘንድ በቤተ ሰቡ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም አገልጋይ ማን ነው? 46ጌታው በመጣ ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ አገልጋይ ብፁዕ ነው። 47እውነት እላችኋለሁ፤ በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 48ነገር ግን ያ ክፉ አገልጋይ በልቡ፣ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ ቢል፣ 49የባልንጀሮቹንም አገልጋዮች መምታት ቢጀምር፣ ከሰካራሞችም ጋራ መብላትና መጠጣት ቢጀምር፣ 50የዚያ አገልጋይ ጌታ ባላሰበው ቀን፣ ባላወቀውም ሰዓት ይመጣል፤ 51ይቈራርጠዋልም፤ ዕድል ፈንታውንም ከግብዞች ጋራ ያደርጋል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”