ዝም አልልም
አንድ ሰው የኢየሩሳሌም ማዳን እስኪታይ ድረስ ዝም ለማለት እምቢ ይላል፤ አብንም ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንዲጨቀጭቁት ጠባቂዎችን ያቆማል። ስሞቿ ይለወጣሉ፤ የተተወች ባድማም ሳይሆን ደስታዬ በእርሷ ናት፣ ባል ያገባች ትባላለች። አብ ሙሽራ በሙሽራይቱ ደስ እንደሚለው በእርሷ ደስ ይለዋል።
62 1ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤ ስለ ኢየሩሳሌምም አላርፍም፤ ጽድቋ እንደ ንጋት፣ ድነቷም እንደሚነድድ ችቦ እስኪበራ ድረስ። 2አሕዛብ ጽድቅሽን፣ ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ አባታችን ራሱ በሚሰጥሽ አዲስ ስም ትጠሪያለሽ። 3በአባታችን እጅ የውበት አክሊል፣ በአባታችን እጅም የንግሥና ዘውድ ትሆኛለሽ። 4ከእንግዲህ የተተወሽ ተብለሽ አትጠሪም፤ ምድርሽም ባድማ ተብላ አትጠራም፤ ነገር ግን ሔፍሲባ—ተድላዬ በእርሷ ነው—ተብለሽ ትጠሪያለሽ፤ ምድርሽም ቤውላ—ያገባች—ትባላለች፤ የአባታችን ልብ በአንቺ ደስ ይለዋልና፤ ምድርሽም ባል ይኖራታል። 5ጐበዝ ድንግልን እንደሚያገባ፣ እንዲሁ ወንዶች ልጆችሽ ያገቡሻል፤ ሙሽራም በሙሽሪት ደስ እንደሚለው፣ እንዲሁ አባትሽ በአንቺ ደስ ይለዋል።
6ኢየሩሳሌም ሆይ፤ በቅጥሮችሽ ላይ ጠባቂዎችን አስቀምጫለሁ፤ ቀኑን ሙሉ ሌሊቱንም ሙሉ ከቶ ዝም አይሉም። እናንተ አባታችንን የምታሳስቡ፣ ለራሳችሁ ዕረፍት አትስጡ፤ 7ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና፣ በምድርም ሁሉ ላይ የተመሰገነች እስኪያደርጋት ድረስ ዕረፍት አትስጡት።
8አባታችን በቀኝ እጁ፣ በኀይለኛ ክንዱም እንዲህ ሲል ማለ፦ “ከእንግዲህ እህልሽን ለጠላቶችሽ መብል አድርጌ አልሰጥም፤ መጻተኞችም የደከምሽበትን አዲስ የወይን ጠጅ አይጠጡትም፤ 9ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል፤ አባታችንንም ያመሰግናሉ፤ የለቀሙትም በመቅደሴ አደባባዮች ይጠጡታል።”
10በበሮች ዐልፉ፣ ዐልፉ! ለሕዝቡ መንገድ አዘጋጁ። አውራ ጎዳናውን ገንቡ፣ ገንቡ፤ ድንጋዮቹን አስወግዱ፤ ለአሕዛብ ዐላማ ከፍ አድርጉ።
11እነሆ፣ አባታችን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ አውጇል፦ ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሉ፤ “እነሆ፣ ድነትሽ ይመጣል፤ እነሆ፣ ዋጋው ከእርሱ ጋር ነው፤ ብድራቱም በፊቱ ነው።” a a v11 ራእይ 22፥12 ይህን መጪውን ይሰይመዋል፤ ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በቶሎ እመጣለሁ፤ ብድራቴንም ከእኔ ጋር አመጣለሁ።”
12እነርሱም ቅዱስ ሕዝብ፣ በአባታችን የተቤዡ ተብለው ይጠራሉ፤ አንቺም የተፈለግሽ፣ ያልተተወች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።