እንደ ማር የጣፈጠው ጥቅልል
ጥቅልሉን በላ፣ እንደ ማርም ጣፈጠው፤ ከዚያም በቴልአቢብ ወዳሉት ምርኮኞች ተወሰደ፣ በመካከላቸውም ደንግጦ ሰባት ቀን ተቀመጠ። አብ ለማስጠንቀቅ ተጠያቂ የሆነ ጠባቂ አደረገው፤ ከዚያም ቃል ሲሰጠው ብቻ እንዲናገር አንደበቱን አሰረው።
3 1እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን ጥቅልል ብላ፤ ከዚያም ሄደህ ለእስራኤል ቤት ተናገር” አለኝ።
2እኔም አፌን ከፈትሁ፤ እርሱም ይህን ጥቅልል እንድበላ ሰጠኝ።
3እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በምሰጥህ በዚህ ጥቅልል ሆድህን መግብ፤ አንጀትህንም ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፋጭ ሆነ።
4ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ወደ እስራኤል ቤት ሄደህ ቃሌን ንገራቸው።
5“ንግግሩ ለማይገባህ፣ ቋንቋውም ለከበደ ሕዝብ አልተላክህምና፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ቤት ነው የተላክኸው፤ 6ቃላቸውን ልትረዳ ወደማትችላቸው፣ ንግግራቸው ለማይገባህና ቋንቋቸው ለከበደ ብዙ ሕዝቦች አልተላክህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ፣ በእርግጥ ይሰሙህ ነበር። 7የእስራኤል ቤት ግን ሊሰሙህ አይፈቅዱም፤ እኔን ሊሰሙ አይፈቅዱምና፤ የእስራኤል ቤት ሁሉ ደንዳና ራስና ግትር ልብ ያላቸው ናቸውና። 8እነሆ፣ ፊትህን እንደ ፊታቸው፣ ግንባርህንም እንደ ግንባራቸው አደነደንሁ። 9ግንባርህን ከጠጠር ይልቅ እንደ ጠነከረ አልማዝ አደረግሁ፤ አትፍራቸው፤ መልካቸውንም አይተህ አትደንግጥ፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና።”
10እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የምነግርህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ያዝ፤ በጆሮህም ስማ። 11ወደ ምርኮኞች፣ ወደ ወገኖችህ ሄደህ ተናገራቸው፤ ይስሙም እምቢ ይበሉም፣ ‘ጌታ አባት እንዲህ ይላል’ ብለህ ንገራቸው።”
12ከዚያም የአባታችን መንፈስ አነሣኝ፤ ከበስተ ኋላዬም፣ “የአባታችን ክብር ከመኖሪያ ስፍራው ይባረክ!” የሚል ታላቅ የመናወጥ ድምፅ ሰማሁ። 13እርስ በእርስ የሚነካኩት የሕያዋን ፍጥረታት ክንፎች ድምፅ፣ በአጠገባቸውም ያሉት መንኰራኵሮች ድምፅ፣ ታላቅ የመናወጥ ድምፅ ነበር። 14መንፈሱም አነሣኝ፤ ወስዶኝም ሄደ፤ እኔም በመረረ መንፈስ ሄድሁ፤ መንፈሴ በውስጤ ይቃጠል ነበር፤ የአባታችንም እጅ በእኔ ላይ በርትቶ ነበር። 15በኮቦር ወንዝ አጠገብ በቴል አቢብ ወዳሉት ምርኮኞች መጣሁ፤ በዚያም በመካከላቸው ተደናግጬ ሰባት ቀን ተቀመጥሁ።
አባታችን ጠባቂ ሾመ
16ከሰባቱ ቀን ፍጻሜ በኋላ፣ የአባታችን ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦
17“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌ ሾምሁህ፤ ከአፌ ቃል በሰማህ ጊዜ ከእኔ ዘንድ አስጠንቅቃቸው። 18ክፉውን ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ፣ አንተም ባታስጠነቅቀው፣ ክፉውም ነፍሱን ለማዳን ከክፉ መንገዱ እንዲመለስ ቃል ተናግረህ ባታስጠነቅቀው፣ ያ ክፉ ሰው በኀጢአቱ ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
19“አንተ ግን ክፉውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከክፋቱ ወይም ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፣ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ።
20“ደግሞም፣ ጻድቅ ሰው ከጽድቁ ተመልሶ በደል ባደረገ ጊዜ፣ እኔም በፊቱ ዕንቅፋት ባኖርሁ ጊዜ፣ ይሞታል። ስላላስጠነቀቅኸው በኀጢአቱ ይሞታል፤ ያደረገውም ጽድቅ አይታሰብም፤ ደሙንም ከእጅህ እፈልጋለሁ። 21አንተ ግን ጻድቁን ኀጢአት እንዳያደርግ ብታስጠነቅቀው እርሱም ባያደርግ፣ ማስጠንቀቂያውን ስለ ሰማ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን ታድናለህ።”
22በዚያም የአባታችን እጅ በእኔ ላይ ነበረ፤ እርሱም፣ “ተነሥተህ ወደ ሜዳ ውጣ፤ በዚያም ከአንተ ጋራ እነጋገራለሁ” አለኝ።
23እኔም ተነሥቼ ወደ ሜዳ ወጣሁ፤ እነሆም፣ በኮቦር ወንዝ አጠገብ እንዳየሁት ክብር፣ የአባታችን ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ።
24መንፈሱም ወደ እኔ ገባ፤ በእግሬም አቆመኝ፤ ተናገረኝም፤ እንዲህም አለኝ፦ “ሄደህ በቤትህ ውስጥ ራስህን ዝጋ። 25አንተም፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ ገመዶችን ያስሩብሃል፤ በእነርሱም ያስሩሃል፤ ስለዚህ በሕዝቡ መካከል መውጣት አትችልም።
26ምላስህን በላንቃህ አጣብቃለሁ፤ ድዳም ትሆናለህ፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና ልትገሥጻቸው አትችልም። 27ከአንተ ጋራ በምነጋገርበት ጊዜ ግን አፍህን እከፍትልሃለሁ፤ አንተም ‘ጌታ አባት እንዲህ ይላል’ ትላቸዋለህ። የሚሰማ ይስማ፤ እምቢ የሚልም እምቢ ይበል፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና።”