የአባታችን ትእዛዛት
በዓመቱ የመጀመሪያ ቀን ሁሉም ነገር ተተከለ፣ ተቀባ፣ በቦታውም ተቀመጠ፤ አሮንና ልጆቹ ታጥበው ልብስ ለበሱ። ከዚያም ደመናው ድንኳኑን ሸፈነ፤ የአብ ክብርም ሙሴ መግባት እስኪያቅተው ድረስ ሞላው። ከዚህ በኋላ መቼ እንደሚጓዙ የሚወስነው ደመናው ነው።
40 1አባታችንም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤
2“ማደሪያውን፣ ማለትም የመገናኛውን ድንኳን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን አቁም። 3የምስክሩን ታቦት በውስጡ አኑር፤ ታቦቱንም በመጋረጃ ጋርደው። 4ገበታውን አግባ፤ በእርሱ ላይ የሚደረገውንም አዘጋጅ፤ መቅረዙን አግባ፤ መብራቶቹንም አብራ። 5የወርቁን የዕጣን መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት አኑር፤ መጋረጃውንም በማደሪያው መግቢያ ላይ አንጠልጥል። 6የሚቃጠለውን መሥዋዕት መሠዊያ በማደሪያው፣ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ፊት አኑር፤ 7ሰኑንም በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑር፤ ውሃም አድርግበት። 8በዙሪያው አደባባዩን አዘጋጅ፤ መጋረጃውንም በአደባባዩ በር ላይ አንጠልጥል።
9“የቅባቱን ዘይት ወስደህ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቅባ፤ እርሱንና ዕቃዎቹን ሁሉ ቀድስ፤ እርሱም የተቀደሰ ይሆናል። 10የሚቃጠለውን መሥዋዕት መሠዊያና ዕቃዎቹን ሁሉ ቅባ፤ መሠዊያውንም ቀድስ፤ መሠዊያውም እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። 11ሰኑንና መቀመጫውን ቅባ፤ ቀድሰውም።
12“ከዚያም አሮንንና ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ አምጣ፤ በውሃም እጠባቸው። 13አሮንን ቅዱሱን ልብስ አልብሰው፤ ካህን ሆኖ ያገለግለኝ ዘንድ ቅባውና ቀድሰው። 14ልጆቹንም አምጣ፤ ቀሚሶችንም አልብሳቸው። 15አባታቸውን እንደ ቀባህ እነርሱንም ቅባ፤ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ። ቅባታቸውም በትውልድ ሁሉ ዘንድ የዘላለም ክህነት ይሆንላቸዋል።”
16ሙሴም አባታችን እንዳዘዘው ሁሉን አደረገ። 17በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በወሩም በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ። 18ሙሴም ማደሪያውን አቆመ፤ መሠረቶቹን አኖረ፤ ሳንቃዎቹን ተከለ፤ መወርወሪያዎቹንም አደረገ፤ ዐምዶቹንም አቆመ። 19ድንኳኑንም በማደሪያው ላይ ዘረጋ፤ የድንኳኑንም መሸፈኛ ከላዩ ላይ አደረገ፤ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው። 20ምስክሩንም ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረ፤ መሎጊያዎቹንም በታቦቱ ላይ አደረገ፤ የስርየቱንም መክደኛ በታቦቱ ላይ አኖረ። 21ታቦቱንም ወደ ማደሪያው አስገባ፤ የመጋረጃውንም መጋረጃ ሰቅሎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ፤ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው። 22ገበታውንም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፣ በማደሪያው በስተ ሰሜን በኩል፣ ከመጋረጃው ውጭ አኖረ፤ 23በእርሱም ላይ ኅብስቱን በአባታችን ፊት አደረደረ፤ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው። 24መቅረዙንም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፣ ከገበታው ትይዩ፣ በማደሪያው በስተ ደቡብ በኩል አኖረ፤ 25መብራቶቹንም በአባታችን ፊት አበራ፤ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው። 26የወርቁንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፣ በመጋረጃው ፊት አኖረ፤ 27በእርሱም ላይ ሽቱ ዕጣን አጠነ፤ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው። 28ከዚያም መጋረጃውን በማደሪያው መግቢያ ላይ አንጠለጠለ። 29የሚቃጠለውንም መሥዋዕት መሠዊያ በማደሪያው፣ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ አኖረ፤ በእርሱም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህል ቍርባን አቀረበ፤ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው። 30ሰኑንም በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኖረ፤ ለመታጠቢያም ውሃ አደረገበት፤ 31ሙሴ፣ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በእርሱ ታጠቡ። 32ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ ወይም ወደ መሠዊያው በቀረቡ ጊዜ ሁሉ ይታጠቡ ነበር፤ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው። 33አደባባዩንም በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ አዘጋጀ፤ መጋረጃውንም በአደባባዩ በር ላይ አንጠለጠለ። እንዲሁም ሙሴ ሥራውን ፈጸመ።
ክብሩ ማደሪያውን ሞላው
34ከዚያም ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፤ የአባታችንም ክብር ማደሪያውን ሞላው። 35ደመናው ከላዩ ስለ ዐረፈ፣ የአባታችንም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላው፣ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ሊገባ አልቻለም። 36ደመናው ከማደሪያው ላይ በተነሣ ጊዜ ሁሉ፣ እስራኤላውያን በጕዞአቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር፤ 37ነገር ግን ደመናው ባልተነሣ ጊዜ፣ እስከ ተነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። 38የአባታችን ደመና በቀን ማደሪያውን ይሸፍን ነበርና፤ በሌሊትም እሳት በውስጡ ነበር፤ ይህም በጕዞአቸው ሁሉ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ይታይ ነበር።