አዛርያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ
የይሁዳው ዓዛርያስ በቈዳ በሽታ ተመትቶ ለብቻው እየኖረ አምሳ ሁለት ዓመት ይነግሣል፤ እስራኤል ግን በአንድ ትውልድ ውስጥ አምስት ነገሥታትን ይፈጃል፤ አብዛኞቹ በተተኳቸው ሰው ተገድለዋል። አሦር ግብር መሰብሰብና የሰሜኑን ክልሎች በሙሉ ማፍለስ ይጀምራል።
15 1የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ አዛርያስ ነገሠ። 2በነገሠ ጊዜ ዐሥራ ስድስት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ። እናቱም ኢየሩሳሌማዊት ይኮልያ ትባል ነበር። 3አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው፣ እርሱም በአባታችን ፊት መልካም የሆነውን አደረገ። 4የኮረብታ መስገጃዎች ግን አልጠፉም፤ ሕዝቡም እስከ አሁን በዚያ ይሠዋና ዕጣን ያጥኑ ነበር። 5አባታችንም ንጉሡን መታው፤ እስከ ሞተበት ቀንም ድረስ የቈዳ በሽታ ይዞት ተለይቶ በሚኖርበት ቤት ኖረ። የንጉሡም ልጅ ኢዮአታም ቤተ መንግሥቱን ይመራ፣ የአገሩንም ሕዝብ ያስተዳድር ነበር። 6የቀረው የአዛርያስ ታሪክ፣ ያደረገውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎ የለምን? 7አዛርያስም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ከእነርሱ ጋራ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮአታም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
የዘካርያስ አጭር ንግሥና በእስራኤል
8የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በሰማርያ በእስራኤል ላይ ስድስት ወር ነገሠ። 9አባቶቹ እንዳደረጉት፣ እርሱም በአባታችን ፊት ክፉ የሆነውን አደረገ። እስራኤልን ኀጢአት ያሠራውን የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት አልተወም። 10የያቤስ ልጅ ሰሎም በእርሱ ላይ አደመ፤ በሕዝቡም ፊት መትቶ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ። 11የቀረው የዘካርያስ ታሪክ በእስራኤል ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎአል።
12ይህም አባታችን ኢዩን፣ “ልጆችህ እስከ አራተኛው ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ” ብሎ የተናገረው ቃል ነበር። እንዲሁም ሆነ።
የሰሎም የአንድ ወር ንግሥና በእስራኤል
13የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የያቤስ ልጅ ሰሎም ነገሠ፤ በሰማርያም አንድ ወር ነገሠ። 14የጋዲ ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወደ ሰማርያ ወጣ፤ በዚያም የያቤስን ልጅ ሰሎምን መትቶ ገደለው፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ። 15የቀረው የሰሎም ታሪክ፣ ያደረገውም አድማ በእስራኤል ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎአል።
16በዚያን ጊዜ ምናሔም ከቴርሳ ጀምሮ ቲፍሳንና በውስጥዋ ያሉትን ሁሉ፣ አገሯንም አጠፋ፤ ደጃፉን ስላልከፈቱለት አጠፋት፤ የፀነሱትንም ሴቶች ሁሉ ሆድ ቀደደ።
ምናሔም በእስራኤል ላይ ነገሠ
17የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በሰማርያም ዐሥር ዓመት ነገሠ። 18በአባታችን ፊት ክፉ የሆነውን አደረገ። በዘመኑም ሁሉ እስራኤልን ኀጢአት ያሠራውን የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት ከቶ አልተወም። 19የአሦር ንጉሥ ፉል በአገሩ ላይ መጣ፤ ምናሔምም መንግሥቱን በእጁ ለማጽናት ፉል እንዲደግፈው ሲል ሠላሳ ስምንት ቶን ያህል ብር ሰጠው። 20ምናሔምም ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ ይህን ገንዘብ ከእስራኤል፣ ከሀብታሞቹም ሰዎች ሁሉ፣ ከእያንዳንዱ አንድ ነጥብ ሁለት ፓውንድ ያህል ብር አስገበረ። ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ተመለሰ፤ በአገሩም አልቈየም። 21የቀረው የምናሔም ታሪክ፣ ያደረገውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎ የለምን? 22ምናሔምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁም ፋቅያስ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
ፋቅያስ በእስራኤል ላይ ነገሠ
23የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በአምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቅያስ በሰማርያ በእስራኤል ላይ መንገሥ ጀመረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ። 24በአባታችን ፊት ክፉ የሆነውን አደረገ። እስራኤልን ኀጢአት ያሠራውን የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት አልተወም። 25የእርሱ አዛዥ የሆነው የረማልያ ልጅ ፋቁሕ በእርሱ ላይ አደመ፤ ከአርጎብና ከአርዮስ፣ ከአምሳ ገለዓዳውያንም ጋራ በሰማርያ በንጉሡ ቤት ምሽግ ውስጥ መታው። ገደለውም፤ በእግሩም ተተክቶ ነገሠ። 26የቀረው የፋቅያስ ታሪክ፣ ያደረገውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎአል።
ፋቁሕ በእስራኤል ላይ ነገሠ
27የይሁዳ ንጉሥ አዛርያስ በነገሠ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የረማልያ ልጅ ፋቁሕ በሰማርያ በእስራኤል ላይ መንገሥ ጀመረ፤ ሃያ ዓመትም ነገሠ። 28በአባታችን ፊት ክፉ የሆነውን አደረገ። እስራኤልን ኀጢአት ያሠራውን የናባጥ ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት አልተወም። 29ፋቁሕ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ፣ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጣ፤ ኢዮንን፣ አቤል ቤትማዓካን፣ ኢያኖሕን፣ ቄዴስን፣ ሐጾርን፣ ገለዓድንና ገሊላን፣ የንፍታሌምንም ምድር ሁሉ ወሰደ፤ ሕዝቡንም ወደ አሦር አፈለሰ። 30ከዚያም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በረማልያ ልጅ በፋቁሕ ላይ አደመ፤ መትቶ ገደለው፤ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በነገሠ በሃያኛው ዓመት በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። 31የቀረው የፋቁሕ ታሪክ፣ ያደረገውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎአል።
ኢዮአታም በይሁዳ ላይ ነገሠ
32የእስራኤል ንጉሥ የረማልያ ልጅ ፋቁሕ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም በይሁዳ ላይ መንገሥ ጀመረ። 33በነገሠ ጊዜ ሃያ አምስት ዓመቱ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ። እናቱም የሳዶቅ ልጅ ይሩሳ ትባል ነበር። 34አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው፣ እርሱም በአባታችን ፊት መልካም የሆነውን አደረገ። 35የኮረብታ መስገጃዎች ግን አልጠፉም፤ ሕዝቡም እስከ አሁን በዚያ ይሠዋና ዕጣን ያጥኑ ነበር። እርሱም የአባታችንን ቤት የላይኛውን በር ሠራ። 36የቀረው የኢዮአታም ታሪክ፣ ያደረገውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ተጽፎ የለምን? 37በዚያ ዘመን አባታችን የሶርያን ንጉሥ ራሲንንና የረማልያን ልጅ ፋቁሕን በይሁዳ ላይ መላክ ጀመረ። 38ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋራ ተቀበረ፤ ልጁም አካዝ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።