ሁሉም ነገር አዲስ ሆነ
አሮጌው ሥርዓት አልፏል፤ አብም ከሰዎች ጋር ሊኖር ይመጣል፤ እርሱ ራሱ አባታቸው ሆኖ እንባቸውን ከፊታቸው ያብሳል። ከተማይቱ ተለክታ፣ በዕንቍ አጊጣ፣ በሁሉም አቅጣጫ በሮች ኖረዋት ትወርዳለች። በውስጧ ቤተ መቅደስ የለም፤ እርሱና በጉ ቤተ መቅደሷ ናቸውና፤ በሮቿንም የሚያዘጋ ሌሊት የለም።
21 1ከዚያም አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የቀደመው ሰማይና የቀደመችው ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ የለም። 2ቅድስቲቱን ከተማ፣ አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአባታችን ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤ ለባልዋ አጊጣ እንደ ተዘጋጀች ሙሽራ ተዘጋጅታ ነበር።
3ከዙፋኑም የመጣ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “እነሆ፣ የአባታችን ማደሪያ ከሰዎች ጋር ነው። ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እርሱ ራሱም አባታቸው ከእነርሱ ጋር ይሆናል።
4አባታችን እንባን ሁሉ ከዐይኖቻቸው ያብሳል፤ ሞትም ከእንግዲህ የለም፤ ልቅሶም ቢሆን ዋይታም ሥቃይም ከእንግዲህ አይኖርም፤ የቀደሙት ነገሮች ዐልፈዋልና።”
5በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው እንዲህ አለ፤ “እነሆ፣ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ።” ደግሞም፣ “ይህን ጻፍ፤ እነዚህ ቃላት የታመኑና እውነተኛ ናቸው” አለ። 6እንዲህም አለኝ፤ “ተፈጸመ። አልፋና ዖሜጋ፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ሰው ከሕይወት ውሃ ምንጭ በነጻ እሰጣለሁ። 7ድል የሚነሣ ሁሉ እነዚህን ይወርሳል፤ እኔም አባቱ እሆናለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል። 8ፈሪዎች ግን፣ የማያምኑ፣ የሚያስጸይፉ፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ዝሙተኞች፣ ጠንቋዮች፣ ጣዖት አምላኪዎችና ውሸታሞች ሁሉ ዕድላቸው በእሳትና በዲን በሚቃጠለው ባሕር ውስጥ ነው፤ ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”
9ሰባቱን የመጨረሻ መቅሰፍቶች የሞሉባቸውን ሰባት ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፣ “ና፤ ሙሽራዪቱን፣ የበጉን የኢየሱስን ሚስት አሳይሃለሁ” አለኝ። 10በመንፈስም ወደ ታላቅና ረጅም ተራራ ወሰደኝ፤ ቅድስቲቱንም ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከአባታችን ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ 11የአባታችንንም ክብር ትገልጥ ነበር፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ዕንቍ፣ እንደ ብርሌ የጠራ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ነበር። 12ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፤ ዐሥራ ሁለት በሮችም ነበሯት፤ በበሮቹም ዐሥራ ሁለት መላእክት ቆመው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች የዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስሞች በእነርሱ ላይ ተጽፈው ነበር፤ 13በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮች፣ በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ። 14የከተማዪቱም ቅጥር ዐሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩት፤ በእነርሱም ላይ የበጉ የኢየሱስ የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ዐሥራ ሁለት ስሞች ነበሩ።
15ከእኔም ጋር የሚነጋገረው ከተማዪቱን፣ በሮችዋንና ቅጥሮችዋን ይለካ ዘንድ የወርቅ መለኪያ ዘንግ ይዞ ነበር። 16ከተማዪቱም አራት ማዕዘን ነበረች፤ ርዝመትዋም ከስፋትዋ ጋር እኩል ነበር። በዘንጉም ለካት፤ 1,400 ማይል ያህል ነበረች፤ ርዝመትዋ፣ ስፋትዋና ከፍታዋ እኩል ነበሩ። 17ቅጥርዋንም ለካ፤ በሰው መለኪያ 216 ጫማ ያህል ነበር፤ ይህም የመልአኩ መለኪያ ደግሞ ነው። 18ቅጥሩም ከኢያሰጲድ ተሠርቶ ነበር፤ ከተማዪቱም እንደ ጥሩ መስተዋት የጠራ ጥሩ ወርቅ ነበረች። 19የከተማዪቱ ቅጥር መሠረቶች በልዩ ልዩ ዕንቍ ሁሉ ተጌጠው ነበር፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣ 20አምስተኛው ሶርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክሪሶላይት፣ ስምንተኛው ቤርሎስ፣ ዘጠነኛው ቶጳዝዮን፣ ዐሥረኛው ክሪሶጵራስዮን፣ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፣ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጥስ ነበር። 21ዐሥራ ሁለቱም በሮች ዐሥራ ሁለት ዕንቍዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱ በር ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበር። የከተማዪቱም መንገድ እንደ ጥሩ መስተዋት የጠራ ጥሩ ወርቅ ነበር።
22በእርሷም ውስጥ መቅደስ አላየሁም፤ ሁሉን ቻይ ጌታ አባትና በጉ ኢየሱስ መቅደስዋ ናቸውና። 23ከተማዪቱም ሊያበሩላት ፀሐይና ጨረቃ አያስፈልጓትም፤ የአባታችን ክብር ያበራላታልና፤ መብራትዋም በጉ ኢየሱስ ነው። 24አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርሷ ያመጣሉ። 25በሮችዋም በቀን ከቶ አይዘጉም፤ በዚያም ሌሊት የለም። 26የአሕዛብንም ክብርና ሞገስ ወደ እርሷ ያመጣሉ። 27ርኩስ የሆነ ነገር ከቶ ወደ እርሷ አይገባም፤ የሚያስጸይፍ ወይም ሐሰተኛ የሆነ ነገር የሚያደርግም ማንም አይገባም፤ በበጉ በኢየሱስ የሕይወት መጽሐፍ ተጽፈው የሚገኙት ብቻ ይገባሉ እንጂ።