የዘገየ ተስፋ፣ የተፈጸመ ምኞት
ገንዘብና ምኞት በውስጡ ያልፋሉ፤ ምንም ሳይኖረው ሀብታም መስሎ ከመታየት ጀምሮ፣ እየቀነሰ እስከሚሄድ ማጭበርበርና በዝግታ እየበዛ እስከሚሄድ ቁጠባ ድረስ። የመጠበቅንም ሕመም ይጠቅሳል፤ የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማልና። ባልንጀሮች ዋጋ አላቸው፦ ከጠቢባን ጋር ተመላለስ፣ ጠቢብም ትሆናለህ።
13 1ጠቢብ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል፤ ፌዘኛ ግን ዘለፋን አይሰማም። 2ሰው ከአንደበቱ ፍሬ መልካም ነገርን ያጣጥማል፤ የከዳተኞች ፍላጎት ግን ግፍ ነው። 3አንደበቱን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል፤ ከንፈሩን የሚያላላ ግን ጥፋት ይደርስበታል። 4ሰነፍ ሰው ይመኛል፤ ነገር ግን ምንም አያገኝም፤ የትጉህ ፍላጎት ግን ፍጹም ይረካል። 5ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤ ክፉ ሰው ግን ነውርንና ውርደትን ያመጣል። 6ጽድቅ መንገዱ ንጹሕ የሆነውን ይጠብቃል፤ ክፋት ግን ኀጢአተኛውን ይገለብጣል። 7አንዱ ሀብታም መስሎ ይታያል፤ ነገር ግን ምንም የለውም፤ ሌላው ድኃ መስሎ ይታያል፤ ነገር ግን ብዙ ሀብት አለው። 8የሰው ሀብት ሕይወቱን ይቤዠዋል፤ ድኃ ግን ዛቻን አይሰማም። 9የጻድቃን ብርሃን በደስታ ያበራል፤ የክፉዎች መብራት ግን ይጠፋል። 10ትዕቢት ጠብን እንጂ ሌላ አያስገኝም፤ ጥበብ ግን ምክርን ከሚፈልጉ ጋራ ናት። 11በማጭበርበር የተገኘ ሀብት ይመናመናል፤ ጥቂት በጥቂት የሚሰበስብ ግን ያበዛዋል። 12የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል፤ የተፈጸመ ምኞት ግን የሕይወት ዛፍ ነው። 13ቃልን የሚንቅ በራሱ ላይ ጥፋትን ያመጣል፤ ትእዛዝን የሚያከብር ግን ይሸለማል። 14የጠቢባን ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ሰውን ከሞት ወጥመድ ያርቃል። 15መልካም ማስተዋል ሞገስን ያስገኛል፤ የከዳተኞች መንገድ ግን ጥፋታቸው ነው። 16አስተዋይ ሰው ሁሉ በዕውቀት ይሠራል፤ ሞኝ ግን ሞኝነቱን ያሳያል። 17ክፉ መልእክተኛ በመከራ ውስጥ ይወድቃል፤ ታማኝ መልእክተኛ ግን ፈውስን ያመጣል። 18ተግሣጽን ለሚንቅ ድኽነትና ውርደት ይደርስበታል፤ ዕርማትን የሚቀበል ግን ይከበራል። 19የተፈጸመ ምኞት ለነፍስ ጣፋጭ ነው፤ ከክፋት መራቅ ግን ለሞኞች አስጸያፊ ነው። 20ከጠቢባን ጋራ የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሞኞች ባልንጀራ ግን ጉዳት ይደርስበታል። 21መቅሰፍት ኀጢአተኞችን ያሳድዳል፤ መልካም ነገር ግን ጻድቃንን ይሸልማል። 22መልካም ሰው ለልጅ ልጆቹ ርስትን ያወርሳል፤ የኀጢአተኛ ሀብት ግን ለጻድቅ ይከማቻል። 23ያልታረሰ የድኆች እርሻ ብዙ ምግብ ሊያስገኝ ይችላል፤ በፍትሕ ማጣት ግን ይጠራረጋል። 24በትርን የሚቆጥብ ልጁን ይጠላል፤ የሚወደው ግን በመገሠጽ ይተጋል። 25ጻድቅ ልቡ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤ የክፉዎች ሆድ ግን ይራባል።