ችኩል ቃላት፣ ፈዋሽ ምላስ
በአብዛኛው ስለ ሥራ፣ ስለ ቃላትና ሌሎች ሰዎች ሊያዩት ስለሚችሉት ነገር ነው። ትጉ እጆች ይገዛሉ፣ ስንፍና ግን በግዳጅ ሥራ ያበቃል፤ የችኮላ ቃላት ይወጋሉ፣ የሐሰት ምላስም ለቅጽበት ብቻ ትኖራለች። በመካከላቸው አንድ ጸጥ ያለ መስመር፦ ጭንቀት ልብን ያከብዳል፣ መልካም ቃል ግን ያነሣዋል።
12 1ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤ ዘለፋን የሚጠላ ግን ደንቆሮ ነው። 2ቸር ሰው ከአባታችን ሞገስ ያገኛል፤ ክፉ የሚያውጠነጥን ሰውን ግን ይኰንናል። 3ማንም በክፋት ጸንቶ አይኖርም፤ የጻድቃን ሥር ግን ከቶ አይነቀነቅም። 4በጎ ሥነ ምግባር ያላት ሚስት የባሏ ዘውድ ናት፤ የምታሳፍር ግን በአጥንቱ ውስጥ እንዳለ መበስበስ ናት። 5የጻድቃን አሳብ ትክክል ነው፤ የክፉዎች ምክር ግን ተንኰል ነው። 6የክፉዎች ቃላት ደም ለማፍሰስ ያደባሉ፤ የቅኖች ንግግር ግን ንጹሓንን ያድናል። 7ክፉዎች ተገልብጠው ይጠፋሉ፤ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። 8ሰው እንደ ማስተዋሉ ይመሰገናል፤ ጠማማ ልቡና ያለው ግን ይናቃል። 9ተዋርዶ አገልጋይ ያለው፣ ታላቅ መስሎ ከሚራብ ይሻላል። 10ጻድቅ ለእንስሳቱ ደኅንነት ያስባል፤ የክፉዎች ርኅራኄ እንኳ ጭካኔ ነው። 11መሬቱን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፤ ከንቱ ነገርን የሚከተል ግን አእምሮ የለውም። 12ክፉዎች የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ፤ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬ ያፈራል። 13ክፉ ሰው በኀጢአተኛ ንግግሩ ይጠመዳል፤ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል። 14ሰው ከአንደበቱ ፍሬ በበጎ ነገር ይጠግባል፤ የእጁም ሥራ ተመልሶ ዋጋ ይከፍለዋል። 15የሰነፍ መንገድ በራሱ ዐይን ትክክል ሆኖ ይታየዋል፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። 16ሰነፍ ቍጣውን ወዲያው ይገልጣል፤ አስተዋይ ግን ስድብን ይታገሣል። 17እውነትን የሚናገር ታማኝ ምስክር ይሰጣል፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይናገራል። 18ችኩል ቃላት እንደ ሰይፍ ይወጋሉ፤ የጠቢብ ምላስ ግን ፈውስን ያመጣል። 19እውነተኛ ከንፈር ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ሐሰተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ብቻ ነው። 20ክፉ በሚያውጠነጥኑ ሰዎች ልብ ተንኰል ይሞላል፤ ሰላምን ለሚያስፋፉ ግን ደስታ አላቸው። 21በጻድቅ ላይ ምንም ክፉ አይደርስበትም፤ ክፉዎች ግን በመከራ ተሞልተዋል። 22ሐሰተኛ ከንፈር ለአባታችን አስጸያፊ ነው፤ በታማኝነት የሚኖሩ ግን ደስታው ናቸው። 23አስተዋይ ዕውቀቱን ለራሱ ይጠብቃል፤ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ይቀዳል። 24ትጉ እጆች ይገዛሉ፤ ስንፍና ግን በግዳጅ ሥራ ይጨርሳል። 25ጭንቀት ልብን ያከብደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል። 26ጻድቅ ባልንጀራውን ይመራል፤ የክፉዎች መንገድ ግን ያስታቸዋል። 27ሰነፍ ያደነውን አይጠብስም፤ ትጉ ሰው ግን ንብረቱን ከፍ አድርጎ ይይዛል። 28በጽድቅ መንገድ ሕይወት አለ፤ በዚያ መንገድም ሞት የለም።