ዳግመኛ ዕድል
የአብ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ይመጣል፤ ዮናስም ሄዶ በነነዌ ውስጥ የአንድ ቀን መንገድ ተጕዞ ከአርባ ቀን በኋላ እንደምትገለበጥ ያውጃል። ከተማይቱ ሁሉ ታምናለች፣ ንጉሡም ዙፋኑን ትቶ ማቅ ለብሶ በአመድ ላይ ይቀመጣል፤ እግዚአብሔርም መመለሳቸውን አይቶ አያጠፋቸውም።
3 1ከዚያም የአባታችን ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፦
2“ተነሥተህ ወደዚያች ታላቅ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የምሰጥህንም መልእክት ዐውጅ።”
3ዮናስም አባታችን እንደ ተናገረው ተነሥቶ ወደ ነነዌ ሄደ። ነነዌም እጅግ ታላቅ ከተማ ነበረች፤ ለማቋረጥም ሦስት ቀን የሚፈጅ ነበር። 4ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማዪቱ ዘልቆ ገባ፤ “ከአርባ ቀናት በኋላ ነነዌ ትገለበጣለች!” እያለ ጮኸ። a a v4 “ትገለበጣለች” የሚለው ቃል ሆን ተብሎ ሁለት ገጽታ ይዟል፤ መጥፋት ወይም መለወጥ ማለት ሊሆን ይችላል፤ ይህም የተቀረው ምዕራፍ የሚፈጽመው ምጸት ነው።
5የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾም ዐወጁ፤ ከታላቁ እስከ ታናሹ ማቅ ለበሱ።
6ዜናው ወደ ነነዌ ንጉሥ በደረሰ ጊዜ፣ ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ በዐመድ ላይ ተቀመጠ። 7በንጉሡና በመኳንንቱ ትእዛዝ በነነዌ ውስጥ እንዲህ ተብሎ ታወጀ፦ ማንም ሰውም ሆነ እንስሳ፣ የከብት መንጋም ሆነ የበግ መንጋ ምንም አይቅመስ፤ አይሰማሩ፤ ውሃም አይጠጡ። 8ሰውም ሆነ እንስሳ ማቅ ይልበሱ፤ ሁሉም በሙሉ ኀይላቸው ወደ እግዚአብሔር ይጩኹ፤ እያንዳንዱም ከክፉ መንገዱና በእጁ ካለው ዐመፅ ይመለስ። 9ማን ያውቃል? ምናልባት እግዚአብሔር ተመልሶ ሐሳቡን ይለውጥ፤ ከጽኑ ቍጣውም ተመልሶ እኛ እንዳንጠፋ ያደርግ ይሆናል።
10እግዚአብሔርም ሥራቸውን አየ፤ ከክፉ መንገዳቸው እንደ ተመለሱም ተመለከተ፤ ሊያመጣባቸው ዝቶ ከነበረው መቅሠፍት ሐሳቡን ለወጠ፤ አላደረገውምም።