አባትህ ስለ አንተ ይዋጋል
ከጦርነት በፊት ካህኑ ሠራዊቱን፣ አብ ከእነርሱ ጋር ስለሚሄድ እንዳይፈሩ ይነግራቸዋል። ከዚያም አንዳንዶቹ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፤ አዲስ ቤት፣ አዲስ የወይን ቦታ ወይም ያጩአት ልጃገረድ ያላቸው፣ ወይም በቀላሉ የፈሩ። ለከተሞች አስቀድሞ ሰላም ይቀርብላቸዋል፤ የሚከብቡ ሠራዊትም እንኳ የፍሬ ዛፎችን መቁረጥ አይፈቀድላቸውም።
20 1ከጠላቶችህ ጋራ ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ፣ ፈረሶችን፣ ሠረገሎችንና ከአንተ የሚበዛ ሠራዊት ባየህ ጊዜ፣ አትፍራቸው፤ ከግብፅ ምድር ያወጣህ አባትህ ከአንተ ጋራ ነውና። 2ወደ ጦርነት ልትገባ ባለህበት ጊዜ፣ ካህኑ ቀርቦ ለሕዝቡ ይናገራል። 3እንዲህም ይላቸዋል፤ “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ ዛሬ ከጠላቶቻችሁ ጋራ ለመዋጋት ትወጣላችሁ፤ ተስፋ አትቁረጡ፣ አትፍሩ፣ አትደንግጡ፣ ከእነርሱም የተነሣ አትሸበሩ፤ 4ከእናንተ ጋራ የሚሄድ፣ ስለ እናንተ ከጠላቶቻችሁ ጋራ ተዋግቶ ድልን የሚሰጣችሁ አባታችሁ ነውና።”
5ከዚያም ሹማምንቱ ለሕዝቡ እንዲህ ይላሉ፤ “አዲስ ቤት ሠርቶ ያልመረቀ ሰው አለን? በጦርነት ሞቶ ሌላ ሰው እንዳይመርቀው ወደ ቤቱ ይመለስ። 6የወይን ተክል ተክሎ ፍሬውን ገና ያልበላ ሰው አለን? በጦርነት ሞቶ ሌላ ሰው እንዳይበላው ወደ ቤቱ ይመለስ። 7ሴት አጭቶ ያላገባት ሰው አለን? በጦርነት ሞቶ ሌላ ሰው እንዳያገባት ወደ ቤቱ ይመለስ።” 8ሹማምንቱም ለሕዝቡ ጨምረው እንዲህ ይላሉ፤ “የሚፈራና የደከመ ልብ ያለው ሰው አለን? የወንድሞቹ ልብ እንደ እርሱ እንዳይቀልጥ ወደ ቤቱ ይመለስ።” 9ሹማምንቱም ለሕዝቡ መናገር በጨረሱ ጊዜ፣ የሚመሯቸውን የሠራዊት አዛዦች ይሾማሉ።
10አንዲትን ከተማ ለመውጋት በቀረብሃት ጊዜ፣ ሰላምን አውጅላት። 11በሰላም መልሳ በሯን ብትከፍትልህ፣ በውስጧ ያለው ሕዝብ ሁሉ ለአንተ ተገዥ ሆኖ በጒልበት ያገለግልሃል። 12ሰላምን እምቢ ብትልና ጦርነት ብትገጥምህ ግን፣ ክበባት። 13አባትህም በእጅህ አሳልፎ በሰጣት ጊዜ፣ በውስጧ ያሉትን ወንዶች ሁሉ በሰይፍ ስለት ፍጃቸው። 14ሴቶቹን፣ ልጆቹን፣ እንስሳቱንና በከተማዋ ውስጥ ያለውን ሁሉ ግን፣ ይኸውም ምርኮዋ ሁሉ፣ ለራስህ ማርከህ ውሰድ፤ አባትህ የሰጠህንም የጠላቶችህን ምርኮ ተጠቀም። 15ከእነዚህ አሕዛብ ከተሞች ውጭ የሆኑትን፣ ከአንተ የራቁትን ከተሞች ሁሉ እንዲህ አድርግ። 16አባትህ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ በእነዚህ ሕዝቦች ከተሞች ውስጥ ግን፣ እስትንፋስ ያለውን ማንኛውንም ነገር በሕይወት አታስቀር። 17ይልቁንም አባትህ እንዳዘዘህ፣ ኬጢያውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፤ 18ይህም ለአማልክቶቻቸው የሚያደርጉትን አስጸያፊ ነገር ሁሉ እንድትከተል እንዳያስተምሩህ፣ በአባትህም ላይ ኀጢአት እንዳታደርግ ነው።
19አንዲትን ከተማ ለመያዝ ስትዋጋ ብዙ ቀን በከበብሃት ጊዜ፣ ዛፎቿን መጥረቢያ በመስደድ አታጥፋ፤ ከእነርሱ ብላ እንጂ አትቍረጣቸው። የሜዳ ዛፍ እንደ ጠላትህ ይቈጠር ዘንድ ሰው አይደለምና። 20ለምግብ እንዳልሆኑ የምታውቃቸውን ዛፎች ብቻ ቍረጥ፤ ይህም ከአንተ ጋራ ጦርነት በገጠመችው ከተማ ላይ እስክትወድቅ ድረስ የከበባ መሣሪያ እንድትሠራ ነው።