የአብያም የተከፈለ ልብ በይሁዳ
አብያም የአባቱን ኀጢአት ደገመ፤ ኢየሩሳሌም ግን ስለ ዳዊት ስትል ጸናች። አሳ የአባታችንን ልብ ፈለገ፤ የገዛ አያቱን የአሼራ ምስል አቃጠለ፤ ሆኖም የአራምን ርዳታ በቤተ መቅደሱ ብር ገዛ። በእስራኤል በኣሻ ናዳብን ገድሎ የኢዮርብዓምን ዘር አጠፋ።
15 1የናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ አብያም በይሁዳ ላይ ነገሠ። 2በኢየሩሳሌምም ሦስት ዓመት ነገሠ። የእናቱም ስም የአቤሴሎም ልጅ መዓካ ነበር። 3ከእርሱ በፊት አባቱ የሠራውን ኀጢአት ሁሉ ደገመ፤ ልቡም እንደ ቅድመ አያቱ እንደ ዳዊት ልብ ለአባታችን ፍጹም አልነበረም። 4ሆኖም አባታችን ስለ ዳዊት ሲል በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው፤ ከእርሱ በኋላ ልጁን በማስነሣት ኢየሩሳሌምንም ጸንታ እንድትኖር አደረገ። 5ዳዊት በአባታችን ፊት መልካም የሆነውን አድርጎ ነበርና፤ ዕድሜውን ሙሉ፣ ከኬጢያዊው ከኡርዮ ነገር በቀር፣ ካዘዘው ሁሉ ፈቀቅ አላለም። 6በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ጦርነት ነበረ። 7የአብያም ሌሎች ሥራዎች፣ ያደረገውም ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ የተጻፉ አይደሉምን? በአብያምና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ቀጠለ። 8አብያምም ከአባቶቹ ጋራ አረፈ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። በእርሱም ፈንታ ልጁ አሳ ነገሠ።
አሳ የአብን ልብ ፈለገ
9የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያኛው ዓመት፣ አሳ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 10በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ። የሴት አያቱም ስም የአቤሴሎም ልጅ መዓካ ነበር። 11አሳ እንደ ቅድመ አያቱ እንደ ዳዊት በአባታችን ፊት መልካም የሆነውን አደረገ። 12ከምድሪቱም የቤተ መቅደስ ወንዶች ዘማዊያንን አባረረ፤ አባቶቹ የሠሩትንም ጣዖታት ሁሉ አስወገደ። 13የሴት አያቱ መዓካ ለአሼራ ርኩስ ምስል ስለ ሠራች ከእቴጌነት ሻራት፤ አሳም ምስሏን ቈርጦ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው። 14የኰረብታ መስገጃዎች ቢቀሩም፣ የአሳ ልብ ግን ዕድሜውን ሙሉ ለአባታችን ፍጹም ነበረ። 15አባቱ የቀደሰውን ቅዱስ ነገር፣ የራሱንም ቅዱስ ስጦታዎች፦ ብሩን፣ ወርቁንና ቅዱሳት ዕቃዎችን ወደ አባታችን ቤት አገባ።
16በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በበኣሻ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ጦርነት ነበረ። 17የእስራኤል ንጉሥ በኣሻ ይሁዳን ለመውጋት ወጣ፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ አንድም ሰው እንዳይወጣና እንዳይገባ ራማን አጸና። 18አሳም በአባታችን ቤት ግምጃ ቤትና በቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ ለአገልጋዮቹ ሰጣቸው። ንጉሡ አሳም በደማስቆ ይገዛ ወደ ነበረው የሶርያ ንጉሥ፣ ወደ ሔዝዮን ልጅ ወደ ጣብሪሞን ልጅ ወደ ቤንሃዳድ እንዲህ የሚል መልእክት ሰደደ፤ 19“በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረ፣ በእኔና በአንተ መካከል ኪዳን ይሁን። ብርና ወርቅ ስጦታ አድርጌ ልኬልሃለሁ። ሂድ፤ የእስራኤል ንጉሥ በኣሻ ከእኔ ዘንድ እንዲሄድ፣ ከእርሱ ጋራ ያለህን ኪዳን አፍርስ።”
20ቤንሃዳድም ንጉሡን አሳን ሰማ፤ የሰራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ላከ። ኢዮንን፣ ዳንን፣ አቤል ቤት መዓካን፣ ኪኔሬትን ሁሉ የንፍታሌምንም ምድር ሁሉ መታ። 21በኣሻም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ራማን ማጽናቱን ተወ፤ በቲርጻም ተቀመጠ። 22ንጉሡ አሳም ለይሁዳ ሁሉ አዋጅ ነገረ፤ አንድም ሰው አልቀረም፤ በኣሻም ራማን ለመሥራት ተጠቅሞበት የነበረውን ድንጋይና እንጨት ተሸከሙ። አሳም በእነርሱ በብንያም ያለችውን ጌባንና ምጽጳን ሠራ። 23የአሳ ሌሎች ሥራዎች፣ ኀይሉ ሁሉ፣ ያደረገውም ሁሉ፣ የሠራቸውም ከተሞች፣ በይሁዳ ነገሥታት ዜና መዋዕል የተጻፉ አይደሉምን? ሆኖም በስተ እርጅናው በእግሮቹ ደዌ ነበረበት። 24አሳም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በቅድመ አያቱም በዳዊት ከተማ ከእነርሱ ጋራ ተቀበረ። በእርሱም ፈንታ ልጁ ኢዮሣፍጥ ነገሠ።
የናዳብ ክፉ ንግሥና በእስራኤል
25የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። 26በአባታችን ፊት ክፉ የሆነውን አደረገ፤ በአባቱ መንገድና እስራኤልን ባሠራው ኀጢአት ተመላለሰ። 27ከይሳኮር ወገን የሆነው የአኪያ ልጅ በኣሻ በእርሱ ላይ አደመ፤ ናዳብና እስራኤል ሁሉ የፍልስጥኤማውያኗን ከተማ ጊበቶንን ከብበው ሳሉ፣ በኣሻ በጊበቶን መታው። 28የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት በኣሻ ገደለው፤ በእርሱም ፈንታ ነገሠ። 29በነገሠም ጊዜ፣ አባታችን በባሪያው በሴሎናዊው በአኪያ በኩል እንደ ተናገረ፣ ሁሉን እስኪያጠፋ ድረስ፣ ትንፋሽ ያለውን አንድም ሳያስቀርለት የኢዮርብዓምን ቤት ሁሉ መታ፤ 30ይህም ኢዮርብዓም ስለ ሠራውና እስራኤልን ስላሠራው ኀጢአት፣ የእስራኤል አምላክ የሆነውን አባታችንን ለቍጣ ስለ አነሣሣ ነበረ።
31የናዳብ ሌሎች ሥራዎች፣ ያደረገውም ሁሉ፣ በእስራኤል ነገሥታት ዜና መዋዕል መጽሐፍ የተጻፉ አይደሉምን? 32በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በበኣሻ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ጦርነት ነበረ።
በኣሻ በእስራኤል ነገሠ
33የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ የአኪያ ልጅ በኣሻ በቲርጻ በእስራኤል ሁሉ ላይ ሃያ አራት ዓመት ነገሠ። 34በአባታችን ፊት ክፉ የሆነውን አደረገ፤ በኢዮርብዓም መንገድና እስራኤልን ባሠራው ኀጢአት ተመላለሰ።