ታላቂቱ ጋለሞታ ተገለጠች
አንድ መልአክ ለዮሐንስ በኢየሱስ ምስክሮች ደም የሰከረች፣ ሐምራዊ የለበሰችና በቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠች ሴት ያሳየዋል። ዮሐንስ ይደነቃል፤ መልአኩም ራሶቹንና ቀንዶቹን ይተረጉምለታል። በመጨረሻም አውሬውና ነገሥታቱ በእርሷ ላይ ተነሥተው ያቃጥሏታል፤ ይህም የአብን ዓላማ ይፈጽማል።
17 1ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፤ “ና፣ በብዙ ውሃዎች ላይ በተቀመጠችው በታላቂቱ ጋለሞታ ላይ የሚመጣውን ፍርድ አሳይሃለሁ። 2የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር ዝሙት ፈጸሙ፤ የምድርም ነዋሪዎች በኀጢአቷ ወይን ሰከሩ።” 3በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ወሰደኝ፤ በዚያም እግዚአብሔርን በሚሰድቡ ስሞች በተሞላ፣ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉት በቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠች ሴት አየሁ። 4ሴቲቱም ሐምራዊና ቀይ ልብስ ለብሳ፣ በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቍዎች ተሽቆጥቍጣ፣ አስጸያፊ ነገሮችና የዝሙቷ ርኩሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ በእጇ ይዛ ነበር። 5በግንባሯም ላይ ምስጢር የሆነ ስም፦ “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የጋለሞቶችና የምድር አስጸያፊ ነገሮች እናት” ተብሎ ተጽፎ ነበር።
6ሴቲቱም በቅዱሳን ደም፣ በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ተደነቅሁ።
7መልአኩም፣ “ለምን ትደነቃለህ? የሴቲቱን፣ እንዲሁም የተሸከማትን፣ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እነግርሃለሁ። 8ያየኸው አውሬ ነበረ፤ አሁን ግን የለም፤ ከጥልቁም ሊወጣ ተዘጋጅቶ ወደ ጥፋቱ ይሄዳል። ስማቸው ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፈ፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎች አውሬውን ባዩ ጊዜ ይደነቃሉ፤ ነበረ፣ የለም፣ ዳሩ ግን ይመጣልና።
9ይህ ጥበብ ያለው አእምሮ ይሻል፤ ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራሮች ናቸው፤ ሰባት ነገሥታትም ናቸው። 10አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላውም ገና አልመጣም፤ በመጣም ጊዜ ጥቂት ጊዜ ሊቈይ ይገባዋል። 11የነበረውና የሌለው አውሬ ራሱ ስምንተኛው ነው፤ ከሰባቱም አንዱ ሆኖ ወደ ጥፋት ይሄዳል። 12ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥት ያልተቀበሉ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣን ይቀበላሉ። 13እነዚህ አንድ ሐሳብ አላቸው፤ ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው አሳልፈው ይሰጣሉ።
14በጉን ይዋጋሉ፤ በጉም ድል ያደርጋቸዋል፤ እርሱ የጌቶች ጌታ የነገሥታትም ንጉሥ ነውና፤ ከእርሱ ጋር ያሉትም የተጠሩ፣ የተመረጡና የታመኑ ናቸው።” 15መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “ጋለሞታዪቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውሃዎች ሕዝቦች፣ ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብና ቋንቋዎች ናቸው። 16ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታዪቱን ይጠላሉ፤ ባድማና ዕራቍቷን ያደርጓታል፤ ሥጋዋንም ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል። 17አባታችን ፈቃዱን እንዲፈጽሙ፣ በአንድ ሐሳብ እንዲተባበሩ፣ የአባታችንም ቃላት እስኪፈጸሙ ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው አሳልፈው እንዲሰጡ በልባቸው ውስጥ አኑሮታልና። a a v17 አውሬውን የሚያገለግሉ ዐመፀኛ ነገሥታት እንኳ የአባታችንን ፈቃድ ይፈጽማሉ። እርሱም ታሪክን ወደ በጉ ድል ይመራል። 18ያየሃት ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሠው ታላቂቱ ከተማ ናት።”