በልዳድ እንደ ገና ተናገረ
የበልዳዶስ የመጨረሻ ንግግር ስድስት ቍጥሮች ብቻ ነው፤ ከርቀት በቀር ምንም አልቀረለትም። ግዛት የእግዚአብሔር ነው፤ ጨረቃና ከዋክብት እንኳ በፊቱ ንጹሓን አይደሉም፤ ታዲያ ሟች ሰው ምንድን ነው? ብል፣ ትል። የወዳጆቹ ክርክር ቃላት አልቆበታል።
25 1ከዚያም ሹሃዊው በልዳድ እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2“ግዛትና ፍርሃት የእርሱ ናቸው፤ በከፍታዎቹ ሰላምን ያደርጋል። 3ሠራዊቱን ሊቈጥር የሚችል ማን አለ? ብርሃኑስ በሁሉ ላይ አይወጣምን? 4ታዲያ ሟች ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? ከሴት የተወለደስ እንዴት ንጹሕ ሊሆን ይችላል? 5እነሆ፣ ጨረቃም እንኳ አያበራም፤ ከዋክብትም በእርሱ ዐይን ንጹሓን አይደሉም፤ 6እጭ የሆነ ሟች ሰውማ እንዴት ይበልጥ፣ ትል የሆነ የሰው ልጅማ እንዴት ይበልጥ!”