አባታችን ኪዳኑን ያድሳል
አዲስ ጽላቶች ተጠርበው በታቦቱ ውስጥ ይቀመጣሉ፤ ሌዊም ተለይቶ አብ ራሱ ርስቱ ይሆንለታል። ከዚያም ጥያቄው ይመጣል፤ አብ ከአንተ ምን ይሻል? እንድትፈራው፣ እንድትወደውና እንድታገለግለው። እርሱ መጻተኛውን ይወዳል፤ ምግብም ይሰጠዋል፤ ስለዚህ እናንተም መጻተኞችን ውደዱ።
10 1በዚያን ጊዜ አባታችን እንዲህ አለኝ፤ “እንደ ፊተኞቹ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርብ፤ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፤ የእንጨት ታቦትም ሥራ። 2አንተ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት በጽላቶቹ ላይ እጽፋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታስቀምጣቸዋለህ።”
3ስለዚህ ከግራር እንጨት ታቦት ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረብሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ። 4አባታችን በጉባኤው ቀን በተራራው ላይ ከእሳቱ መካከል ለእናንተ የተናገረውን ዐሥርቱን ትእዛዛት፣ እንደ ቀድሞው በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፤ አባታችንም ሰጠኝ። 5ተመልሼ ከተራራው ወረድሁ፤ ጽላቶቹንም በሠራሁት ታቦት ውስጥ አስቀመጥሁ፤ አባታችን እንዳዘዘኝም በዚያ ይገኛሉ።
6እስራኤላውያን ከብኤሮት ብኔ ያዕቃን ተነሥተው ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም በዚያ ሞተ፣ በዚያም ተቀበረ፤ ልጁ አልዓዛርም በእርሱ ፈንታ ካህን ሆኖ አገለገለ። 7ከዚያም ወደ ጉድጎዳ ተጓዙ፤ ከጉድጎዳም ወደ ዮጥባታ፣ ወደ ውሃ ምንጮች ምድር ተጓዙ። 8በዚያን ጊዜ አባታችን የኪዳኑን ታቦት እንዲሸከም፣ በፊቱ እንዲቆም፣ እንዲያገለግለውና በስሙ እንዲባርክ የሌዊን ነገድ ለየ፤ እስከ ዛሬም ድረስ እንዲሁ ያደርጋሉ። 9ስለዚህ ሌዊ ከወንድሞቹ ጋራ ድርሻም ርስትም የለውም፤ አባታችን ተስፋ እንደ ሰጠው፣ አባታችን ራሱ ርስቱ ነው።
10እኔም እንደ ፊተኛው ጊዜ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በተራራው ላይ ቈየሁ፤ አባታችንም እንደ ገና ሰማኝ፤ አባታችን ሊያጠፋህ አልፈለገም።
11አባታችንም እንዲህ አለኝ፤ “ተነሥተህ በሕዝቡ ፊት ሂድ፤ ለአባቶቻቸው ልሰጣቸው የማልሁትን ምድር ገብተው እንዲወርሱ።”
አባታችን ከአንተ የሚሻው
12አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አባታችን ከአንተ የሚሻው ትፈራው ዘንድ፣ በመንገዱ ሁሉ ትሄድ ዘንድ፣ ትወድደው ዘንድ፣ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ታገለግለው ዘንድ፣ 13ዛሬ ስለ መልካምህ የማዝህን የአባታችንን ትእዛዛትና ሥርዐቶቹን ትጠብቅ ዘንድ እንጂ ሌላ ምንድን ነው? 14እነሆ፣ ሰማያት፣ የሰማያት ሰማይ፣ ምድርና በውስጧ ያለ ሁሉ የአባታችን ናቸው። 15ነገር ግን አባታችን አባቶችህን ወደደ፤ ከእነርሱም በኋላ ዘራቸውን፣ ይኸውም እናንተን ከሕዝቦች ሁሉ በላይ መረጠ፤ ዛሬም እንዲሁ ነው። 16ስለዚህ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፤ ዐንገታችሁንም ከእንግዲህ ወዲያ አታደንድኑ። a a v16 “የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ” የሚለው፣ ልብን እምቢተኛና ዝግ የሚያደርገውን ሁሉ ቈርጦ ማስወገድንና ለአባታችን ፈጽሞ መክፈትን ያመለክታል። 17አባታችን የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ ታላቅ፣ ኀያልና የተፈራ አምላክ ነውና፤ ፊትም አያደላም፣ ጕቦም አይቀበልም። 18ለድኻ አደጉና ለመበለቲቱ ፍትሕ ያደርጋል፤ መጻተኛውንም ይወድዳል፣ ምግብና ልብስም ይሰጠዋል። 19እናንተም በግብፅ ምድር መጻተኞች ነበራችሁና መጻተኛውን ውደዱ። 20አባታችንን ፍራ፤ አገልግለው፤ በእርሱም ተጠጋ፤ በስሙም ማል። 21ዓይኖችህ ያዩአቸውን እነዚህን ታላላቅና የሚያስፈሩ ነገሮች ያደረገልህ፣ ምስጋናህ እርሱ ነው፤ አባትህ እርሱ ነው። 22አባቶችህ ሰባ ነፍስ ሆነው ወደ ግብፅ ወረዱ፤ አሁን ግን አባታችን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንድትበዛ አድርጎሃል።