የአባታችን እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ
ፍልስጥኤማውያን የማረኩትን የአብን ታቦት በዳጎን አጠገብ አኖሩት፤ አምላካቸውንም ሁለት ጊዜ በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት፤ በሁለተኛው ጊዜ ራሱና እጆቹ ተቆርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር። ታቦቱ ከአዛጦን ወደ ጌት፣ ከዚያም ወደ አቃሮን ሲሄድ እባጭና ሽብር ተከተለው፤ ከተማ ሁሉ ከእርሱ እንዲገላገል ለመነ።
5 1ፍልስጥኤማውያን የአባታችንን ታቦት ማርከው ከአቤንኤዘር ወደ አዛጦን አመጡት። 2ፍልስጥኤማውያን የአባታችንን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤተ መቅደስ አግብተው በዳጎን አጠገብ አኖሩት። 3የአዛጦን ሰዎች በማግስቱ ማልደው ሲነሡ፣ ዳጎን በአባታችን ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፍቶ መሬት ላይ ወድቆ ነበር። ዳጎንንም አንሥተው ወደ ስፍራው መለሱት። 4በማግስቱ ማልደው በተነሡ ጊዜ፣ ዳጎን እንደ ገና በአባታችን ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፍቶ መሬት ላይ ወድቆ ነበር። በዚህ ጊዜ ራሱና ሁለቱ እጆቹ ተሰብረው በደፉ ላይ ተገኙ፤ ገላው ብቻ ቀረ። 5ስለዚህ እስከ ዛሬ ድረስ የዳጎን ካህናትም ሆኑ በአዛጦን ወዳለው የዳጎን ቤተ መቅደስ የሚገቡ ሁሉ የዳጎንን ደፍ አይረግጡም። 6የአባታችን እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ እጅግ ከበደ። እነርሱንም አጠፋ፤ አዛጦንንና በዙሪያዋ ያለውን ግዛት በእባጭ መታ። 7የአዛጦን ሰዎች ይህን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ጋራ አይቀመጥ፤ እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ከብዷል” አሉ። 8የፍልስጥኤማውያንን ገዦች ሁሉ ሰብስበው፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ምን እናድርገው?” ብለው ጠየቁ። እነርሱም፣ “የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት ይዛወር” ብለው መለሱ። ስለዚህ የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደዚያ አዛወሩ።
9ከዘዋወሩት በኋላ፣ የአባታችን እጅ በዚያች ከተማ ላይ ደግሞ መጣ፤ እጅግ ታላቅ ድንጋጤም ሆነ። ትንሹንም ትልቁንም የከተማይቱን ሰዎች መታ፤ እባጭም ወጣባቸው። 10ስለዚህ የአባታችንን ታቦት ወደ አቃሮን ሰደዱ። ነገር ግን ታቦቱ እንደ ደረሰ፣ የአቃሮን ሰዎች፣ “እኛንና ወገኖቻችንን ሊገድሉ የእስራኤልን አምላክ ታቦት ወደ እኛ አመጡ!” ብለው ጮኹ።
11ስለዚህ የፍልስጥኤማውያንን ገዦች ሁሉ ሰብስበው፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ሰድዱት፤ እኛንና ወገኖቻችንን እንዳይገድል ወደ ስፍራው ይመለስ” አሉ። የሞት ድንጋጤ ከተማይቱን ሁሉ ይዞ ነበርና፤ የአባታችን እጅ በዚያ እጅግ ከብዶ ነበር። 12ያልሞቱትም በእባጭ ተመቱ፤ የከተማይቱም የእርዳታ ጩኸት ወደ ሰማይ ወጣ።