ትምክሕተኛው ምላስ
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት ማሕሌት። ኤዶማዊው ዶይቅ ወደ ሳኦል መጥቶ፣ “ዳዊት ወደ አኪሜሌክ ቤት ገብቷል” ብሎ ባመለከተው ጊዜ።
ካህናቱን ለሳኦል ያሳበቀውን ዶይቅን የሚመለከት። የሚያጠፋ ቃልን የሚወድና በገዛ ሀብቱ የሚታመን ሰው ተብሎ ይጠራል፤ ከድንኳኑም እንደሚነቀል ይነገረዋል — ዘማሪው ግን በአብ ቤት እንደ ወይራ ዛፍ ያድጋል።
52 1ኀያል ሆይ፣ ስለ ክፋት ለምን ትመካለህ? የአባታችን ምሕረት ቀኑን ሙሉ ጸንቶ ይኖራል።
2ምላስህ ጥፋትን ያውጠነጥናል፤ አንተ አታላይ ሆይ፣ እንደ ተሳለ ምላጭ ነው። 3ከመልካም ይልቅ ክፋትን ትወዳለህ፤ እውነትን ከመናገር ይልቅ ውሸትን ትወዳለህ።
4አንተ ተንኰለኛ ምላስ፣ አጥፊውን ቃል ሁሉ ትወዳለህ። 5አባታችን ግን ለዘላለም ያፈርስሃል፤ ነጥቆ ከድንኳንህ ይነቅልሃል፤ ከሕያዋን ምድርም ሥር ነቅሎ ያጠፋሃል።
6ጻድቃን አይተው ይፈራሉ፤ በእርሱም እየሳቁ እንዲህ ይላሉ፤ 7“ይህን ሰውዬ ተመልከቱ፤ አባታችንን መጠጊያው አላደረገም፤ ነገር ግን በታላቅ ሀብቱ ታምኗል፤ ሌሎችንም በማጥፋት በርትቷል።” 8እኔ ግን በአባታችን ቤት ውስጥ እንደ ለመለመ የወይራ ዛፍ ነኝ፤ ለዘላለም ዘላለም በአባታችን ምሕረት እታመናለሁ። 9ስላደረግኸው ነገር ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፤ በቅዱሳንህ ፊት በስምህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ መልካም ነውና።