ሕዝቦች ወደ አባታችን ተራራ ይጎርፋሉ
አሕዛብ ለመማር ወደ አብ ተራራ ይወጣሉ፤ ሰይፎቻቸውንም ማረሻ አድርገው ይቀጠቅጣሉ፤ እያንዳንዱም ሳይፈራ ከገዛ ወይኑ በታች ይቀመጣል። ከዚያም ዕይታው ወደ አሁኑ ጊዜ ይመለሳል፤ ጽዮን በምጥ ላይ ናት፤ ወደ ባቢሎን ትወጣለች፤ ከጕዞውም አትታደግም፤ ነገር ግን በዚያ ትድናለች።
4 1በመጨረሻው ዘመን የአባታችን ቤት የቆመበት ተራራ ከተራሮች ሁሉ በላይ ጸንቶ ይቆማል፤ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጎርፋሉ። 2ብዙ ሕዝቦች መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፣ ወደ አባታችን ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ መንገዶቹን ያስተምረን ዘንድ፣ በጎዳናዎቹም እንሄድ ዘንድ።” ትምህርት ከጽዮን፣ የአባታችንም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና። 3በብዙ ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ ርቀው ላሉ ኀያላን መንግሥታትም ፍርድ ይሰጣል። ሰይፎቻቸውን ማረሻ፣ ጦሮቻቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም ለጦርነት አይለማመዱም። 4እያንዳንዱ ከገዛ ወይኑ በታች፣ ከገዛ በለሱም በታች ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም፤ የሰማይ ሠራዊት አባት ራሱ ተናግሯልና። 5ሕዝቦች ሁሉ በየራሳቸው አምላክ ስም ይመላለሳሉና፤ እኛ ግን ለዘላለም እስከ ዘላለም በአባታችን ስም እንመላለሳለን።
አባታችን የተበተኑ ልጆቹን ይሰበስባል
6በዚያ ቀን፣ ይላል አባታችን፣ አንካሶችን እሰበስባለሁ፤ የተባረሩትንም፣ ያስጨነቅኋቸውንም አንድነት እሰበስባለሁ። 7አንካሶችን ቀሪ ሕዝብ፣ ርቀው የተጣሉትንም ኀያል ሕዝብ አደርጋለሁ፤ አባታችንም በጽዮን ተራራ ላይ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም ይነግሣቸዋል።
8አንተም የመንጋ ግንብ፣ የጽዮን ልጅ ኮረብታ ሆይ፣ ወደ አንተ ይመጣል፤ የቀድሞው ግዛት፣ የኢየሩሳሌም ልጅ መንግሥት ይመለሳል።
9አሁን ለምን ትጮኺያለሽ? በመካከልሽ ንጉሥ የለምን? እንደ ምጥ ላይ ያለች ሴት ምጥ ይይዝሽ ዘንድ መካርሽ ጠፍቷልን? 10የጽዮን ልጅ ሆይ፣ እንደ ምጥ ላይ ያለች ሴት ተጨነቂ፣ አቃስቺ፤ አሁን ከከተማ ትወጫለሽና በሜዳ ላይ ትኖሪያለሽ፤ ወደ ባቢሎንም ትሄጃለሽ። በዚያ ትድኛለሽ፤ በዚያ አባታችን ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል።
11አሁን ብዙ ሕዝቦች በአንቺ ላይ ተሰብስበው እንዲህ ይላሉ፤ “ትርከስ፤ ዓይኖቻችንም በጽዮን ላይ ደስ ይበላቸው።” 12እነርሱ ግን የአባታችንን ሐሳብ አያውቁም፤ ዕቅዱንም አያስተውሉም፤ እንደ ነዶ ወደ አውድማ እንደ ሰበሰባቸው። 13የጽዮን ልጅ ሆይ፣ ተነሥተሽ ውቂ፤ ቀንድሽን ብረት፣ ሰኰናዎችሽንም ናስ አደርጋለሁና፤ ብዙ ሕዝቦችን ትቀጠቅጫለሽ፤ ትርፋቸውንም ለአባታችን፣ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ትቀድሻለሽ።