የአባታችን ማስጠንቀቂያ፦ በምድሪቱ ኑሩ
የጭፍራ አለቆቹ የሚመጣውን መልስ ሁሉ እንደሚታዘዙ ምለው ኤርምያስ እንዲጸልይ ለመኑት። ከአሥር ቀን በኋላ የአብ ቃል መጣ፤ ብትቀመጡ ትተከላላችሁ፣ ትጠበቃላችሁም፤ ወደ ግብፅ ብትሄዱ ግን የምትፈሩት ሰይፍና ራብ በዚያ ይከተላችኋል። እነርሱ ግን አስቀድመው ወስነው ነበር።
42 1የጦር አዛዦች ሁሉ ከቃሬ ልጅ ከዮሐናንና ከሆሣያ ልጅ ከዮዛንያ ጋር፣ ከታናሽ እስከ ታላቅ ሕዝቡ ሁሉ ቀርበው፣ 2ነቢዩን ኤርምያስን እንዲህ አሉት፤ “ልመናችንን እባክህ ስማ፤ ስለ እኛ፣ ስለዚህ ቀሪ ሁሉ ወደ አባትህ ጸልይ፤ እንደምታየው ከብዙ ጥቂቶች ሆነን ቀርተናልና፣ 3አባትህም የምንሄድበትን መንገድ የምናደርገውንም ነገር ያሳየን ዘንድ ነው።”
4ነቢዩ ኤርምያስም እንዲህ አላቸው፤ “ሰማኋችሁ፤ እንደ ጠየቃችሁት ወደ አባታችሁ እጸልያለሁ፤ አባታችሁም የሚመልሰውን ሁሉ ምንም ሳልሰውር እነግራችኋለሁ።”
5እነርሱም ኤርምያስን እንዲህ አሉት፤ “አባትህ ልትነግረን የሚልክህን ሁሉ ባናደርግ፣ አባታችን በእኛ ላይ እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን። 6መልካም ቢሆን ክፉ፣ ወደ እርሱ የምንልክህን የአባታችንን ድምፅ እንታዘዛለን፤ የአባታችንን ድምፅ ስንታዘዝ መልካም ይሆንልን ዘንድ ነው።”
7ከዐሥር ቀን በኋላም የአባታችን ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። 8እርሱም የቃሬን ልጅ ዮሐናንን፣ ከእርሱ ጋር የነበሩትን አዛዦች ሁሉ፣ ከታናሽ እስከ ታላቅ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ፣
9እንዲህም አለ፤ “ልመናችሁን አቀርብ ዘንድ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አባታችን እንዲህ ይላል፤
10በዚህ ምድር በእውነት ብትኖሩ፣ አፈርሳችሁ ዘንድ ሳይሆን እሠራችኋለሁ፤ ነቅዬ ሳይሆን እተክላችኋለሁ፤ ባመጣሁባችሁ መቅሠፍት ተጸጽቻለሁና።
11አሁን የምትፈሩትን የባቢሎንን ንጉሥ አትፍሩ፤ እርሱን አትፍሩ ይላል አባታችን፤ ላድናችሁና ከእጁ ላስጥላችሁ ከእናንተ ጋር ነኝና።
12ርኅራኄንም አሳያችኋለሁ፤ የባቢሎን ንጉሥ ይራራላችሁ ዘንድ ወደ ምድራችሁም ይመልሳችሁ ዘንድ ነው።
13ነገር ግን የአባታችሁን ድምፅ ባለመታዘዝ፣ ‘በዚህ ምድር አንኖርም’ ብትሉ፣ 14‘አይሆንም፤ ጦርነት ወደማናይበት፣ የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማበት፣ እንጀራም ወደማንራብበት ወደ ግብፅ ሄደን በዚያ እንኖራለን’ ብትሉ፣ 15እናንተ የይሁዳ ቀሪዎች ሆይ፣ የአባታችንን ቃል ስሙ፤ የሰማይ ሰራዊት አባት፣ የእስራኤል አባት እንዲህ ይላል፤ ወደ ግብፅ ሄዳችሁ በዚያ ለመኖር ፊታችሁን ካቀናችሁ፣ 16የምትፈሩት ሰይፍ በግብፅ ይደርስባችኋል፤ የምትፈሩትም ራብ በግብፅ ይከተላችኋል፤ በዚያም ትሞታላችሁ። 17በግብፅ ለመኖር የወሰኑ ሁሉ በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር ይሞታሉ፤ ከማመጣባቸው መቅሠፍት የሚተርፍ ወይም የሚያመልጥ አይኖርም።
18የሰማይ ሰራዊት አባት፣ የእስራኤል አባት እንዲህ ይላል፤ ቍጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ እንደ ፈሰሰ፣ እናንተ ወደ ግብፅ ስትገቡ መዓቴ እንዲሁ በእናንተ ላይ ይፈስሳል፤ የመርገም፣ የድንጋጤ፣ የመሳለቅና የውርደት ነገር ትሆናላችሁ፤ ይህችንም ስፍራ ዳግመኛ አታዩም።”
19“እናንተ የይሁዳ ቀሪዎች ሆይ፣ አባታችን፦ ‘ወደ ግብፅ አትሂዱ’ ብሎ ተናግሯችኋል፤ ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ እወቁ። 20በገዛ ነፍሳችሁ ዋጋ ራሳችሁን አሳሳታችሁ፤ ‘ስለ እኛ ወደ አባታችን ጸልይ፤ የሚለውንም ሁሉ ንገረን እኛም እናደርጋለን’ ብላችሁ ወደ አባታችሁ ልካችሁኝ ነበርና። 21ዛሬም ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን ልነግራችሁ ከላከኝ ነገር በአንዳች የአባታችሁን ድምፅ አልታዘዛችሁም። 22እንግዲህ ለመኖር በምትፈልጉበት ስፍራ በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር እንደምትሞቱ በእርግጥ እወቁ።”