የአባታችን ክብር ቤቱን ሞላ
እሳት ይወርዳል፤ ክብርም ቤቱን ይሞላል፤ ሕዝቡም በንጣፉ ላይ በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዳሉ። ከዚያም አባታችን በሌሊት ቃሉን ይመልሳል፤ ልጆቼ ራሳቸውን ቢያዋርዱ፣ ቢጸልዩ፣ ፊቴን ቢፈልጉና ከክፉ ቢመለሱ እሰማለሁ፣ ይቅር እላለሁ፣ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።
7 1ሰሎሞን ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ፣ እሳት ከሰማይ ወረደ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና መሥዋዕቶቹን በላ፤ የአባታችንም ክብር ቤቱን ሞላው። 2የአባታችን ክብር ስለሞላው፣ ካህናቱ ወደ አባታችን ቤት መግባት አልቻሉም። 3እስራኤላውያን ሁሉ እሳቱ ሲወርድና የአባታችንን ክብር በቤቱ ላይ ባዩ ጊዜ፣ በድንጋዩ ንጣፍ ላይ ፊታቸውን ወደ ምድር አድርገው ተንበረከኩ፤ አባታችንንም እያመለኩና እያመሰገኑ፣ “እርሱ ቸር ነው፤ ምሕረቱ ለዘላለም ይኖራል” አሉ።
4ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በአባታችን ፊት መሥዋዕት አቀረቡ። 5ንጉሥ ሰሎሞን ሃያ ሁለት ሺህ በሬዎችንና መቶ ሃያ ሺህ በጎችን ሠዋ፤ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የአባታችንን ቤት ቀደሱ። 6ካህናቱ በየቦታቸው ቆሙ፤ ሌዋውያኑም ንጉሥ ዳዊት አባታችንን ለማመስገን የሠራቸውን የአባታችንን የሙዚቃ መሣሪያዎች ይዘው ቆሙ፤ ዳዊት በመሣሪያዎቹ አማካይነት በሚያመሰግንበት ጊዜ “ምሕረቱ ለዘላለም ይኖራልና” እያለ ያመሰግን ነበር። በፊታቸውም ካህናቱ መለከቶቹን ነፉ፤ እስራኤልም ሁሉ ቆመ።
7ሰሎሞንም በአባታችን ቤት ፊት ለፊት ያለውን የአደባባዩን መካከል ቀደሰ፤ የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባንንና ስቡን ሊይዝ ስላልቻለ፣ የሚቃጠሉትንና የደኅንነት መሥዋዕቶችን ስብ በዚያ አቀረበ።
8በዚያም ጊዜ ሰሎሞን በዓሉን ሰባት ቀን አከበረ፤ ከሌቦ ሐማት ጀምሮ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ የተሰበሰበ እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆነ እስራኤል ሁሉ ከእርሱ ጋር ነበር። 9የመሠዊያውን መቀደስ ሰባት ቀን በዓሉንም ሰባት ቀን ካከበሩ በኋላ፣ በስምንተኛው ቀን የመዝጊያ ጉባኤ አደረጉ። 10በሰባተኛውም ወር በሃያ ሦስተኛው ቀን፣ አባታችን ለዳዊት፣ ለሰሎሞንና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው መልካም ነገር ደስ ብሏቸውና በልባቸው ተደስተው ሕዝቡን ወደየቤታቸው አሰናበታቸው።
አባታችን ለሰሎሞን ተናገረ
11ሰሎሞንም የአባታችንን ቤትና የንጉሡን ቤተ መንግሥት ፈጸመ፤ ሰሎሞን በአባታችን ቤትና በገዛ ቤቱ ለማድረግ በልቡ ያሰበውን ሁሉ በተሳካ ሁኔታ አከናወነ።
12ከዚያም አባታችን በሌሊት ለሰሎሞን ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህን ስፍራ ለእኔ የመሥዋዕት ቤት እንዲሆን መርጫለሁ።
13“ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማዩን ብዘጋ፣ ወይም ፌንጣ ምድሪቱን እንዲበላ ባዝዝ፣ ወይም በልጆቼ መካከል ቸነፈር ብሰድድ፣ 14ስሜ የተጠራባቸው ልጆቼ ራሳቸውን ቢያዋርዱ፣ ቢጸልዩ፣ ፊቴን ቢፈልጉ፣ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፣ እኔ ከሰማይ እሰማለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፤ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። 15አሁንም ዐይኖቼ ይከፈታሉ፤ ጆሮዎቼም በዚህ ስፍራ ለሚቀርበው ጸሎት ያደምጣሉ። 16አሁንም ስሜ በዚያ ለዘላለም እንዲኖር ይህን ቤት መርጬ ቀድሻለሁ፤ ዐይኖቼና ልቤም ሁልጊዜ በዚያ ይሆናሉ።
17አንተም፣ አባትህ ዳዊት እንደ ተመላለሰ በፊቴ ብትመላለስ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ብታደርግ፣ ሥርዓቴንና ፍርዶቼንም ብትጠብቅ፣ 18“አባትህ ከዳዊት ጋር ኪዳን እንዳደረግሁ፣ ‘የአንተ የሆነ ሰው ሁልጊዜ በእስራኤል ላይ ይገዛል’ ብዬ የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።”
19“ነገር ግን ዘወር ብትሉ፣ የሰጠኋችሁን ሥርዓቴንና ትእዛዛቴን ብትተዉ፣ ሄዳችሁም ሌሎች አማልክትን ብታገለግሉና ብታመልኩ፣ 20እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድሬ እነቅላቸዋለሁ፤ ለስሜ የለየሁትን ይህን ቤተ መቅደስ ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ በአሕዛብ ሁሉ መካከልም ለምሳሌና ለመዘባበቻ አደርገዋለሁ።” 21እጅግ ከፍ ከፍ ያለው ይህ ቤት፣ በአጠገቡ የሚያልፍ ሁሉ ይደነግጣል፤ እንዲህም ይላል፤ “እግዚአብሔር ለዚህ ምድርና ለዚህ ቤት ይህን ለምን አደረገ?
22ሰዎችም መልሰው እንዲህ ይላሉ፤ ‘እነርሱ ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን እግዚአብሔርን፣ የአባቶቻቸውን አምላክ ትተው፣ ሌሎች አማልክትን ተከትለው፣ ሰግደውላቸውና አገልግለዋቸው ነበርና፤ ይህን ጥፋት ሁሉ በእነርሱ ላይ ያመጣባቸው ስለዚህ ነው።’ ”