ለአብ ስም የሚሠራ ቤት
ዳዊትን ይወድድ የነበረው የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለአባታችን ስም ለሚሠራው ቤት ዕንጨትና የእጅ ባለሙያዎችን ላከ፤ ሰሎሞንም በምላሹ ስንዴና ዘይት ላከለት፤ ሁለቱ ነገሥታትም ቃል ኪዳን ተጋቡ። ይህን ሁሉ ፈልፍሎ ለማጓጓዝ ሰሎሞን በፈረቃ የሚሠሩ በዐሥር ሺዎች የሚቈጠሩ እስራኤላውያንን በግዳጅ መለመለ።
5 1የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ሰሎሞን በአባቱ ፋንታ ንጉሥ ሆኖ እንደ ተቀባ በሰማ ጊዜ፣ አገልጋዮቹን ላከለት፤ ኪራም ዳዊትን ሁልጊዜ ይወድደው ነበርና። 2ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ ብሎ መልእክት ላከ፤ 3አባቴ ዳዊት ለአባታችን ስም ቤት ሊሠራ እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ፤ አባታችን ጠላቶቹን ከእግሩ ጫማ በታች እስኪያደርግ ድረስ፣ ጦርነት በየአቅጣጫው ከብቦት ነበርና። 4አሁን ግን አባቴ በየአቅጣጫው ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ባላጋራም የለ፣ መቅሠፍትም የለ።
5አባታችን ለአባቴ ለዳዊት በገባው ቃል መሠረት፣ ለአባቴ ስም ቤት ልሠራ አስቤአለሁ፤ “በፋንታህ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ ለስሜ ቤቱን ይሠራል።”
6ስለዚህ ከሊባኖስ የዝግባ ዛፎች እንዲቈረጡልኝ አድርግ። አገልጋዮቼ ከአገልጋዮችህ ጋራ ይሠራሉ፤ አንተ የምትወስነውንም ዋጋ ሁሉ እከፍልሃለሁ፤ ከእኛ መካከል እንደ ሲዶናውያን ዕንጨት የሚቈርጥ አለመኖሩን አንተ ታውቃለህና።
7ኪራምም የሰሎሞንን ቃል በሰማ ጊዜ፣ እጅግ ደስ አለው፤ እንዲህም አለ፤ “በዚህ ታላቅ ሕዝብ ላይ ለዳዊት ጥበበኛ ልጅ የሰጠ እግዚአብሔር ዛሬ ይባረክ።” 8ኪራምም ወደ ሰሎሞን እንዲህ ብሎ ላከ፤ “መልእክትህን ሰማሁ፤ በዝግባና በጥድ ዕንጨት የምትፈልገውን ሁሉ አደርግልሃለሁ። 9አገልጋዮቼ ግንዶቹን ከሊባኖስ ወደ ባሕር ያወርዳሉ፤ እኔም እንደ ታንኳ አስተሳስሬ በባሕር ላይ ወደ ምትመድበው ስፍራ አንሳፍፋቸዋለሁ፤ በዚያም እፈታቸዋለሁ፤ አንተም ትወስዳቸዋለህ። አንተም ለቤተ ሰቤ ምግብ በማቅረብ ፍላጎቴን ትፈጽማለህ።”
10ስለዚህ ኪራም ሰሎሞን የፈለገውን የዝግባና የጥድ ዕንጨት ሁሉ ሰጠው፤ 11ሰሎሞንም ለኪራም ቤተ ሰብ ዓመት ዓመት ወደ 120,000 የሚጠጋ መስፈሪያ ስንዴ፣ ወደ 120 የሚጠጋ መስፈሪያ የተጨመቀ ዘይትም ይሰጥ ነበር። 12አባታችንም እንደ ገባው ቃል ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው። በኪራምና በሰሎሞን መካከል ሰላም ነበረ፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ተዋዋሉ።
13ንጉሥ ሰሎሞንም ከእስራኤል ሁሉ የሥራ ሰዎች አስነሣ፤ የተመለመሉትም ሠላሳ ሺህ ሰዎች ነበሩ። 14በየወሩም በፈረቃ ዐሥር ሺህ ሰዎችን ወደ ሊባኖስ ይልክ ነበር፤ አንድ ወር በዚያ፣ ሁለት ወር በቤታቸው ይቈዩ ነበር። አዶኒራም የሥራ ሰዎቹን ይቈጣጠር ነበር። 15ሰሎሞንም ሸክም የሚሸከሙ ሰባ ሺህ፣ በተራራማው ምድር ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩት፤ 16ከእነዚህም ሌላ፣ ሥራውን የሚቈጣጠሩና ሠራተኞቹን የሚመሩ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ የሰሎሞን አለቆች ነበሩ። 17በንጉሡም ትእዛዝ የቤቱን መሠረት በተጠረበ ድንጋይ ለመመሥረት፣ ታላላቅና ውድ ድንጋዮችን ፈለጡ። 18የሰሎሞንና የኪራም ግንበኞች፣ የጌባልም ሰዎች፣ ቤቱን ለመሥራት ዕንጨቱንና ድንጋዩን ጠረቡ፤ አዘጋጁም።