ንጉሡ ደስ ይለዋል
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
ሕዝቡ ሕይወትን ለምኖ ያገኘውን፣ በበረከት ብዛት የተቀበለውንና የወርቅ ዘውድ የተቀዳጀውን ንጉሥ ያከብራሉ። መተማመኑ በራሱ ሥራ ላይ ሳይሆን በአብ በመታመን ላይ ያርፋል፤ የአብ እጅም በእርሱ ላይ የሚያሤሩትን ሁሉ ታገኛቸዋለች።
21 1አባታችን ሆይ፣ በኀይልህ ንጉሡ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህ እጅግ ሐሤት ያደርጋል! 2የልቡን መሻት ሰጥተኸዋል፤ ከንፈሮቹ የለመኑህንም አልከለከልኸውም። 3በበረከት ብዛት ልትቀበለው መጥተሃልና፤ በራሱ ላይ ጥሩ የወርቅ ዘውድ አኖርህ። 4ሕይወትን ለመነህ፤ አንተም ሰጠኸው — የዘመን ርዝመትን ለዘላለም እስከ ዘላለም። a a v4 ለዳዊታዊው ንጉሥ የተሰጠው “ለዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖር ሕይወት” ስጦታ፣ ሞት ሊይዘው ባልቻለው በትንሣኤው ንጉሥ በኢየሱስ ፍጻሜውን ያገኛል። 5በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው፤ ግርማንና ልዕልናን ታጐናጽፈዋለህ። 6በእርግጥ የማያልቅ በረከትን ሰጥተኸዋል፤ በፊትህ ደስታም አስደሰትኸው። 7ንጉሡ በአባታችን ይታመናልና፤ በልዑሉ በማይጓደል ፍቅር፣ አባታችን፣ አይናወጥም።
8እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ትይዛለች፤ ቀኝህ የሚጠሉህን ትይዛለች። 9በተገለጥህ ጊዜ እንደሚነድድ እቶን ታደርጋቸዋለህ። አባታችን በቍጣው ይውጣቸዋል፤ እሳቱም ይበላቸዋል። 10ዘራቸውን ከምድር ታጠፋለህ፤ ልጆቻቸውንም ከሰው ዘር መካከል። 11ክፉን ቢያሤሩብህ፣ ተንኰልንም ቢያውጠነጥኑ አይሳካላቸውም። 12ፍላጻህን ወደ ፊታቸው ስታነጣጥር ጀርባቸውን እንዲሰጡ ታደርጋቸዋለህና።
13አባታችን ሆይ፣ በኀይልህ ከፍ ከፍ በል! ኀይልህን እንዘምራለን፤ እናመሰግናለንም።