ስሙን አመስግኑ
በማስረጃ ላይ የተገነባ ውዳሴ፤ አብ በባሕርና በሰማይ የወደደውን ሁሉ ያደርጋል፣ ግብፅን መታ፣ ሴዎንንና ዐግን አወረደ፣ ምድራቸውንም አሳልፎ ሰጠ። ከዚያ ጋር ሲነጻጸሩ ከንቱ አፍና ዓይን ያላቸው ጣዖታት ሠሪዎቻቸውን እንደ እነርሱው ባዶ ያደርጓቸዋል።
135 1ሃሌ ሉያ! የአባታችንን ስም አመስግኑ፤ እናንተ የአባታችን አገልጋዮች፣ አመስግኑት፤ 2በአባታችን ቤት የምታገለግሉ፣ በአባታችን ቤት አደባባዮች ያላችሁ ሆይ።
3አባታችንን አመስግኑ፣ አባታችን መልካም ነውና፤ ስሙን በዝማሬ አመስግኑ፣ ያማረ ነውና። 4አባታችን ያዕቆብን ለራሱ፣ እስራኤልንም ለክብሩ ርስት መርጦአልና።
5አባታችን ታላቅ እንደ ሆነ፣ ሉዓላዊው አባታችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ እንደ ሆነ እኔ ዐውቃለሁና። 6አባታችን የወደደውን ሁሉ በሰማያትና በምድር፣ በባሕሮችና በጥልቆቻቸው ሁሉ አድርጎአል። 7ከምድር ዳርቻ ደመናትን ያወጣል፤ ለዝናብ መብረቅን ያደርጋል፤ ነፋስንም ከመዛግብቱ ያወጣል።
8የግብፅን በኵራት፣ ሰውንም እንስሳንም መታ። 9ግብፅ ሆይ፣ በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ሁሉ ላይ ምልክቶችንና ድንቆችን በመካከልሽ ላከ። 10ብዙ ሕዝቦችን መታ፣ ኀያላን ነገሥታትንም ገደለ፤ 11የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሆንን፣ የባሳንን ንጉሥ ዐግንም፣ የከነዓንንም መንግሥታት ሁሉ፤ 12ምድራቸውንም ርስት አድርጎ፣ ለሕዝቡ ለእስራኤል ርስት አድርጎ ሰጠ።
13አባታችን ሆይ፣ ስምህ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ አባታችን ሆይ፣ መጠራትህ ለትውልድ ሁሉ ነው። 14አባታችን ለሕዝቡ ፍርድን ያመጣልና፣ ለአገልጋዮቹም ይራራልና።
15የአሕዛብ ጣዖታት ብርና ወርቅ፣ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። 16አፍ አላቸው፣ ነገር ግን መናገር አይችሉም፤ ዐይን አላቸው፣ ነገር ግን ማየት አይችሉም፤ 17ጆሮ አላቸው፣ ነገር ግን መስማት አይችሉም፤ በአፋቸውም ውስጥ እስትንፋስ የለም። 18የሚሠሩአቸው እንደ እነርሱ ይሆናሉ፤ በእነርሱ የሚታመኑ ሁሉም እንዲሁ ናቸው።
19የእስራኤል ቤት ሆይ፣ አባታችንን ባርኩ፤ የአሮን ቤት ሆይ፣ አባታችንን ባርኩ፤ 20የሌዊ ቤት ሆይ፣ አባታችንን ባርኩ፤ አባታችንን የምትፈሩ ሆይ፣ አባታችንን ባርኩ። 21በኢየሩሳሌም የሚኖረው አባታችን፣ ከጽዮን የተባረከ ይሁን። ሃሌ ሉያ!