ዋስትናና ተስፋዎች
አራት እርስ በርስ ያልተያያዙ ማስጠንቀቂያዎች። ለባልንጀራህ በችኮላ ከገባኸው ዋስትና ወዲያውኑ ውጣ። ከአልጋህ መነሣት ካቃተህ ጉንዳንን ተመልከት። በዓይኑ የሚጠቅስና በምልክት የሚናገር ሁከት ፈጣሪን ተጠንቀቅ። አብ የሚጠላቸው ሰባት ነገሮች። ከዚያም ደግሞ ምንዝር፣ በጉያህ እንደ ተሸከምከው እሳት።
6 1ልጄ ሆይ፣ ለባልንጀራህ ዋስ ከሆንህ፣ ለእንግዳ ሰውም በእጅ መጨባበጥ ቃል ከገባህ፣ 2በአፍህ ቃል ተጠምደሃል፤ በአፍህ ቃልም ተይዘሃል። 3እንግዲህ ልጄ ሆይ፣ አሁን በባልንጀራህ እጅ ስለ ወደቅህ፣ ራስህን ለማስለቀቅ ይህን አድርግ፤ ሄደህ ራስህን አዋርደህ ባልንጀራህን ለምን። 4ለዐይኖችህ እንቅልፍ አትስጥ፤ ለሽፋሽፍትህም መሽለብን አትስጥ። 5እንደ ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፣ እንደ ወፍም ከወጥመድ አጥማጅ እጅ ራስህን አስለቅቅ።
6አንተ ሰነፍ፣ ወደ ጕንዳን ሂድ፤ መንገዶቿን ተመልከት፤ ጠቢብም ሁን። 7አለቃ፣ ሹም ወይም ገዥ ሳይኖራት፣ 8በበጋ እንጀራዋን ታዘጋጃለች፤ በመከርም ምግቧን ትሰበስባለች።
9አንተ ሰነፍ፣ እስከ መቼ ተኝተህ ትቀራለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? 10ጥቂት እንቅልፍ፣ ጥቂት መሽለብ፣ ለማረፍም እጆችን ጥቂት አጣጥፎ መቀመጥ፣ 11ድኽነትም እንደ ወንበዴ ይመጣብሃል፤ ችጋርም እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።
12የማይረባ ሰው፣ ክፉ ሰው፣ በጠማማ ንግግር ይመላለሳል፤ 13በዐይኖቹ ይጠቅሳል፤ በእግሮቹ ይጠቁማል፤ በጣቶቹም ያመለክታል፤ 14በጠማማ ልቡ ክፋትን ያስባል፤ ዘወትርም ጠብን ይዘራል፤ 15ስለዚህ መቅሠፍት በድንገት ይመጣበታል፤ በቅጽበትም ያለ መድኃኒት ይሰበራል።
16አባታችን የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ ሰባቱም ለእርሱ አስጸያፊዎች ናቸው፦ 17ትዕቢተኛ ዐይኖች፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደምን የሚያፈስሱ እጆች፣ 18ክፉ አሳብን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት ለመሮጥ የሚቸኩሉ እግሮች፣ 19ሐሰትን የሚተነፍስ የሐሰት ምስክር፣ በወንድማማቾችም መካከል ጠብን የሚዘራ ሰው ናቸው።
የአባትህ ቃላት፣ ጋሻህ
20ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው። 21ሁልጊዜ በልብህ ላይ እሰራቸው፤ በዐንገትህም ዙሪያ አስራቸው። 22በምትሄድበት ጊዜ ይመሩሃል፤ በምትተኛበትም ጊዜ ይጠብቁሃል፤ ከእንቅልፍህም በምትነቃበት ጊዜ ያነጋግሩሃል። 23ትእዛዝ መብራት፣ ትምህርትም ብርሃን ነውና፤ የተግሣጽም ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነው፤ 24ከክፉይቱ ሴት ይጠብቅህ ዘንድ፤ ከአመንዝራዪቱም ሴት ለስላሳ ምላስ ይጠብቅህ ዘንድ ነው።
25ውበቷን በልብህ አትመኝ፤ በሽፋሽፍቷም አትማረክ፤ 26የጋለሞታ ዋጋ አንድ እንጀራ ብቻ ነውና፤ ያገባች ሴት ግን ክቡርን ሕይወት ታጠምዳለች። 27ሰው እሳትን በደረቱ አጠገብ ተሸክሞ፣ ልብሱ ሳይቃጠል ይቀራልን? 28ወይስ ሰው በጋለ ፍም ላይ ሄዶ፣ እግሮቹ ሳይቃጠሉ ይቀራሉን? 29ከባልንጀራው ሚስት ጋር የሚተኛም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ ከቅጣት አያመልጥም።
30ሌባ በራበው ጊዜ ነፍሱን ለማጥገብ ቢሰርቅ፣ ሰዎች አይንቁትም፤ 31ተይዞ ቢገኝ ግን ሰባት እጥፍ ይከፍላል፤ የቤቱንም ንብረት ሁሉ ይሰጣል። 32የሚያመነዝር ሰው አእምሮ የለውም፤ ይህን የሚያደርግም ራሱን ያጠፋል። 33ቍስልና ውርደት ያገኘዋል፤ ነውሩም አይደመሰስም።
34ቅናት ሰውን ያስቈጣዋልና፤ በበቀል ቀንም ምሕረትን አያደርግም። 35ምንም ዓይነት ካሳ አይቀበልም፤ ጕቦው ቢበዛም እምቢ ይላል።