በደስታ የሚሰጥ ሰው
ጳውሎስ አካይያ ዝግጁ እንደ ሆነች ለመቄዶንያ አስቀድሞ ተመክቶ ነበር፤ ስለዚህ ሰዎችን አስቀድሞ ይልካል። ስጦታው በግፊት ተጨምቆ ሳይሆን በፈቃድ እንዲሰጥ ይፈልጋል፤ ምክንያቱም አባታችን በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል፤ ደግሞም ገንዘቡ የቆሮንቶስ ሰዎች ፈጽሞ በማያገኟቸው ሰዎች መካከል ምስጋና ይሆናልና።
9 1ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልገኝም፤ 2ዝግጁነታችሁን ዐውቃለሁና፤ አካይያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተዘጋጅታለች እያልሁ ስለ እናንተ ለመቄዶንያ ሰዎች እመካለሁ፤ ቅንዓታችሁም ከእነርሱ አብዛኞቹን አነሣሥቷል። 3ስለዚህ እንደ ተናገርሁት ተዘጋጅታችሁ እንድትገኙ፣ በዚህ ነገር ስለ እናንተ የተመካንበት ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ። 4ያለዚያ የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋራ መጥተው ሳትዘጋጁ ቢያገኙአችሁ፣ በእንዲህ ያለ መተማመን እኛ—እናንተንስ ሳንጠቅስ—እናፍር ነበር። 5ስለዚህ ወንድሞቹ ቀድመው ወደ እናንተ እንዲሄዱና ተስፋ የገባችሁትን ለጋስ ስጦታ አስቀድመው እንዲያዘጋጁ ልማልዳቸው አስፈላጊ ሆኖ አገኘሁት፤ ይኸውም በግዴታ እንደ ተሰጠ ሳይሆን በፈቃደኝነት እንደ ተሰጠ ስጦታ ዝግጁ ይሆን ዘንድ ነው።
6ይህን ዐስቡ፤ በጥቂቱ የሚዘራ በጥቂቱ ደግሞ ያጭዳል፤ በልግስና የሚዘራም በልግስና ያጭዳል። 7እያንዳንዱ በልቡ እንደ ቈረጠ ይስጥ እንጂ በኀዘን ወይም በግድ አይስጥ፤ አባታችን በደስታ የሚሰጠውን ይወድዳልና። 8አባታችን በሁሉ ነገር ሁልጊዜ የሚያስፈልጋችሁ ሁሉ ኖሯችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትበዙ፣ ጸጋውን ሁሉ አትረፍርፎ ሊሰጣችሁ ይችላል። 9ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ “ለድኾች ሰጥቶ በትኗል፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል።”
10ለዘሪ ዘርን ለመብልም እንጀራን የሚሰጥ እርሱ ዘራችሁን ይሰጣል፤ ያበዛላችሁማል፤ የጽድቃችሁንም መከር ያሳድጋል። 11ለልግስና ሁሉ በሁሉ ነገር ትበለጽጋላችሁ፤ ይህም በእኛ በኩል ለአባታችን ምስጋናን ያስገኛል። 12የምታከናውኑት ይህ አገልግሎት የቅዱሳንን ጕድለት ይሞላል ብቻ ሳይሆን፣ ለአባታችን በሚቀርብ በብዙ ምስጋናም ይበዛል። 13በዚህ አገልግሎት ተፈትናችሁ በመገኘታችሁ፣ የክርስቶስን ወንጌል በመመስከር ለምታሳዩት መታዘዝ፣ ከእነርሱና ከሌሎች ሁሉ ጋራ ስለ ልግስናችሁ ሰዎች አባታችንን ያከብራሉ። 14አባታችን ስለ ሰጣችሁ ከሁሉ የላቀ ጸጋ የተነሣ፣ ስለ እናንተ በሚያደርጉት ጸሎት ይናፍቁአችኋል። 15ስለማይነገር ስጦታው አባታችን ይመስገን!