ረባት ወደቀች፤ ዳዊትም ዘውዱን ደፋ
ዳዊት ቤቱ ሲቀር ኢዮአብ በራባት ይዋጋል፤ በዚህ ግን ንጉሡ ዘውዱን ለመውሰድ ይመጣል። ከዚያም ከፍልስጥኤማውያን ግዙፎች ጋር ሦስት ግጭቶች ይከተላሉ፤ ከእነርሱም መካከል እስራኤልን የተገዳደረውና በዳዊት የወንድም ልጅ የተገደለው ስድስት ጣት ያለው ሰው ይገኝበታል።
20 1ዓመቱ ሲዞር፣ ነገሥታት ወደ ጦርነት በሚዘምቱበት ወቅት፣ ኢዮአብ ሠራዊቱን አስከትቶ ወጣ፤ የአሞናውያንንም ምድር አጠፋ፤ መጥቶም ረባትን ከበበ፤ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀረ። ኢዮአብም ረባትን መትቶ አፈረሳት። 2ዳዊትም ዘውዱን ከንጉሣቸው ራስ ላይ ወሰደ። ክብደቱም ሰባ አምስት ፓውንድ ያህል ወርቅ ነበር፤ በከበረ ድንጋይም ተጌጦ ነበር፤ በዳዊትም ራስ ላይ ተደረገ። ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። 3በውስጧ የነበሩትንም ሰዎች አስወጥቶ በመጋዝ፣ በብረት ዶማና በመጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው። ዳዊትም በአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
ግዙፋኑ በእስራኤል እጅ ወደቁ
4ከዚህ በኋላ በጌዝር ከፍልስጥኤማውያን ጋራ ጦርነት ተነሣ። በዚያን ጊዜ ሑሳታዊው ሲበኮይ ከረፋ ዘሮች አንዱን ሲፔይን ገደለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተገዙ።
5ዳግመኛም ከፍልስጥኤማውያን ጋራ ጦርነት ተነሣ። የያዕር ልጅ ኤልሐናን የጌትዊው የጎልያድን ወንድም ልሕሚን ገደለ፤ የጦሩም ዘንግ እንደ ታላቅ የእንጨት ግንድ ወፍራም ነበር። 6እንደ ገናም በጌት ጦርነት ተነሣ፤ በዚያም እጅግ ግዙፍ የሆነ ሰው ነበር፤ በእያንዳንዱ እጁ ስድስት ጣቶች፣ በእያንዳንዱም እግሩ ስድስት ጣቶች፣ በጠቅላላው ኻያ አራት ነበሩት፤ እርሱም ደግሞ ለረፋ የተወለደ ነበር። 7እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ፣ የዳዊት ወንድም የሳማ ልጅ ዮናታን መትቶ ገደለው። 8እነዚህ በጌት ለረፋ የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትና በባሪያዎቹም እጅ ወደቁ።