ከዐውሎ ነፋስ በፊት ተሰብሰቡ
ጥሪው የአብ ቍጣና ትእዛዝ ሳይደርስ እንዲሰበሰቡ ነው፤ የቀረበውም ብቸኛ ተስፋ 'ምናልባት' ነው፤ ትሕትናን ፈልጉ፤ ምናልባት ትሰወሩ ይሆናል። ከዚያም በዙሪያ ያሉት አሕዛብ አንድ በአንድ ይጠራሉ፤ በራሷ የተማመነችው ትዕቢተኛዋ ነነዌም ፍርስራሽ ሆና በመጨረሻ ትቀራለች።
2 1ተሰብሰቡ፤ ተሰባሰቡ፤ አንተ የማታፍር ሕዝብ ሆይ፤ 2ዐዋጁ ሳይወልድ፣ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፣ የአባታችን የሚነድ ቍጣ ሳይመጣባችሁ፣ የአባታችን የቍጣ ቀን ሳይደርስባችሁ። 3ፍርዱን የምታደርጉ፣ የምድር ትሑታን ሁላችሁ፣ አባታችንን ፈልጉ፤ ጽድቅን ፈልጉ፤ ትሕትናን ፈልጉ። ምናልባት በአባታችን የቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል። 4ጋዛ የተተወች ትሆናለችና፣ አስቀሎንም ባድማ ትሆናለች፤ አሽዶድ በቀትር ትባረራለች፣ አቃሮንም ትነቀላለች። 5በባሕር ዳር የምትኖሩ፣ የኪሬታውያን ሕዝብ ሆይ፣ ወዮላችሁ! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፣ የአባታችን ቃል ይቃወምሻል፦ “ነዋሪ እስከማይቀር ድረስ አጠፋሻለሁ።” 6የባሕሩ ዳርቻ የማሰማሪያ ስፍራ ይሆናል፤ ለእረኞች መሰማሪያ፣ ለመንጎችም ጕረኖ ይሆናል። 7ዳርቻውም ለይሁዳ ቤት ቀሪዎች ይሆናል፤ በዚያ ያሰማራሉ፤ ማታም በአስቀሎን ቤቶች ይተኛሉ፤ አባታችን ይጐበኛቸዋልና፣ ብልጽግናቸውንም ይመልስላቸዋልና። 8የሞዓብን ስድብ፣ የአሞናውያንንም ዘለፋ ሰምቻለሁ፤ በእነዚያ ሕዝቤን ተሳድበዋል፣ በድንበራቸውም ላይ ተመክተዋል።
9ስለዚህ፣ የሰማይ ሠራዊት አባት፣ የእስራኤል አባታችን እንዲህ ይላል፤ በሕይወቴ እምላለሁ፤ ሞዓብ እንደ ሰዶም፣ አሞናውያንም እንደ ገሞራ ይሆናሉ፤ የኩርንችትና የጨው ጕድጓድ ምድር፣ ለዘላለምም ባድማ ይሆናሉ። የሕዝቤ ቀሪዎች ይበዘብዟቸዋል፣ የሕዝቤም ተራፊዎች ይወርሷቸዋል። 10“ይህ ስለ ትዕቢታቸው የሚያገኛቸው ነው፤ ሕዝቡን ተሳድበዋልና፣ በሕዝቡም ላይ ተመክተዋልና፤ ይህውም የሰማይ ሠራዊት አባት ሕዝብ ነውና። 11አባታችን በእነርሱ ላይ የሚያስፈራ ይሆናል፤ የምድርን አማልክት ሁሉ ያስራባቸዋልና፤ የአሕዛብም ደሴቶች ሁሉ፣ እያንዳንዱ ከስፍራው ሆኖ ይሰግዱለታል።”
12እናንተ ኢትዮጵያውያንም ደግሞ በሰይፌ ትገደላላችሁ።
13እጁንም ወደ ሰሜን ይዘረጋል፤ አሦርንም ያጠፋል፤ ነነዌንም ባድማ ያደርጋታል፣ እንደ በረሓም ደረቅ ትሆናለች። 14መንጎች በመካከሏ ይተኛሉ፣ የምድረ በዳ አራዊትም ሁሉ፤ ጕጕትና ጃርት በምሰሶቿ ራስ ላይ ያድራሉ። በመስኮቶች ውስጥ ድምፅ ያቀነቅናል፣ በመድረክም ላይ ፍርስራሽ ይሆናል፤ የዝግባው ሥራ ተራቍቷልና። 15ተድላ የሞላባት፣ በእርጋታ የኖረች ከተማ ይህች ናት፤ በልቧም እንዲህ ያለች፤ “እኔ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ማንም የለም።” እንዴት ባድማ ሆነች፣ ለአራዊትም ማደሪያ! በአጠገቧ የሚያልፍ ሁሉ ያፍጫል፣ እጁንም ያወዛውዛል።