ለጢሞቴዎስ፣ እውነተኛ ልጄ
ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን ስለ ማደራጀትና ጤናማ ትምህርትን ስለ መጠበቅ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ የሰጠው የእረኝነት ምክር።
1 1በአዳኛችን በአባታችንና በተስፋችን በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፣ 2በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፤ ከአባታችንና ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ይሁን።
የአብን ቤተ ሰብ ጠብቅ
3ወደ መቄዶንያ ስሄድ እንደ ለመንሁህ፣ አንዳንዶች የተለየ ትምህርት እንዳያስተምሩ ልትመክራቸው በኤፌሶን ቈይ፤ 4ለተረትና መጨረሻ ለሌለው የትውልድ ሐረግም ራሳቸውን እንዳይሰጡ ምከራቸው፤ እነዚህ በእምነት ከሚገኘው ከአባታችን መጋቢነት ይልቅ ክርክርን ያስነሣሉና። 5የዚህ ትእዛዝ ግብ ከንጹሕ ልብ፣ ከበጎ ሕሊናና ከቅን እምነት የሚመነጭ ፍቅር ነው። 6አንዳንዶች ከእነዚህ ስተው ወደ ከንቱ ንግግር ዘወር ብለዋል፤ 7የሚናገሩትን ወይም አጥብቀው የሚያረጋግጡትን ሳያስተውሉ፣ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ ይፈልጋሉ።
8ሕግ በአግባቡ ቢሠራበት መልካም እንደ ሆነ አሁን እናውቃለን፤ 9ይህንም እናውቃለን፤ ሕግ የተሠራው ለጻድቅ ሳይሆን፣ ለዐላውያንና ለዐመፀኞች፣ ለክፉዎችና ለኀጢአተኞች፣ ለርኩሳንና እግዚአብሔርን ለማያከብሩ፣ አባቶቻቸውንና እናቶቻቸውን ለሚመቱ፣ ለነፍሰ ገዳዮች፣ 10ለሴሰኞች፣ ከወንድ ጋራ ለሚተኙ ወንዶች፣ ሰውን ለሚሸጡ ነጋዴዎች፣ ለውሸታሞች፣ በሐሰት ለሚምሉ፣ እንዲሁም ጤናማውን ትምህርት ለሚቃወም ለማናቸውም ነገር ነው፤ 11ይህም አደራ የተሰጠኝ፣ ከቡሩኩ አባታችን የተገኘው የክብር ወንጌል እንደሚለው ነው።
የአብ ምሕረት እጅግ ለከፋው ኀጢአተኛ ደረሰ
12ለአገልግሎቱ ስለ ሾመኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፣ ኀይልን ለሰጠኝ ለጌታችን ለክርስቶስ ኢየሱስ አመሰግናለሁ። 13ቀድሞ እግዚአብሔርን ተሳድቤ ነበር፤ ሌሎችንም አሳድጄ ጨካኝም ነበርሁ፤ ነገር ግን ባለማወቅና በእምነት ጕድለት ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ። 14የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካለው እምነትና ፍቅር ጋራ ለእኔ አትረፈረፈ። 15ይህ ቃል የታመነና ሙሉ በሙሉ ሊቀበሉት የሚገባ ነው፤ ክርስቶስ ኢየሱስ ኀጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ፤ ከእነርሱም እጅግ የከፋሁ እኔ ነኝ። 16ነገር ግን ምሕረትን ያገኘሁት ስለዚህ ነው፤ ክርስቶስ ኢየሱስ እጅግ በከፋሁት በእኔ ላይ ፍጹም ትዕግሥቱን ሊያሳይ፣ ለዘላለም ሕይወት በእርሱ ለሚያምኑ ምሳሌ እንድሆን ነው። 17ለዘመናት ንጉሥ፣ ለማይሞተው፣ ለማይታየው፣ ብቸኛ አምላክ ለሆነው ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ውዳሴ ይሁን፤ አሜን።
መልካሙን ገድል ተጋደል
18ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ፤ ቀድሞ ስለ አንተ በተነገሩት ትንቢቶች መሠረት ይህን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ በእነርሱም መልካሙን ገድል እንድትጋደል ነው፤ 19እምነትንና በጎ ሕሊናን ጠብቅ። አንዳንዶች እነዚህን ጥለው እምነታቸውን እንደ መርከብ ሰብረዋል፤ 20ከእነዚህም መካከል ሑሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው፤ እነርሱንም እግዚአብሔርን እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጠኋቸው።