አብ የኤዶምን የጥንት ጥላቻ ይፈርዳል
በሴይር ተራራ ያለው ኤዶም የጥንት ጥላቻ ይዞ በመከራ ቀን እስራኤልን ለሰይፍ አሳልፎ ሰጠ፤ ከዚያም ባዶ የቀሩትን ሁለቱን አገሮች የራሱ አደረገ። አብ ባዶ የሚሆነው ኤዶም እንደ ሆነ፣ ለዘለቄታውም እንደ ሆነ ይመልሳል።
35 1የአባታችን ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦
2የሰው ልጅ ሆይ፣ ፊትህን በሴይር ተራራ ላይ አዙር፤ በእርሱም ላይ ትንቢት ተናገር። 3እንዲህ በለው፦ ጌታ አባታችን እንዲህ ይላል፦ “ሴይር ተራራ ሆይ፣ እነሆ፣ በአንተ ላይ ነኝ፤ እጄንም በአንተ ላይ እዘረጋለሁ፤ ባድማና ምድረ በዳ አደርግሃለሁ። 4ከተሞችህን ፍርስራሽ አደርጋለሁ፤ አንተም ባድማ ትሆናለህ። እኔም አብ እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
5የጥንት ጥላቻ ስለ ያዝህ፣ የእስራኤልንም ሕዝብ በጥፋታቸው ጊዜ፣ የመጨረሻው ቅጣታቸው በመጣበት ጊዜ ለሰይፍ አሳልፈህ ስለ ሰጠህ፣” 6ስለዚህ፣ ሕያው ነኝና፣ ይላል ጌታ አባታችን፣ ለደም ማፍሰስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ ደምም ያሳድድሃል። ደም ማፍሰስን ስላልጠላህ፣ ደም ያሳድድሃል። 7“ሴይር ተራራን የተፈታ ባድማ አደርገዋለሁ፤ ከእርሱም የሚመጣውንና የሚሄደውን ሁሉ አጠፋለሁ። 8ተራራዎቹን በታረዱት ሰዎች እሞላለሁ፤ በኰረብቶችህ፣ በሸለቆዎችህና በጅረቶችህ ሁሉ በሰይፍ የተገደሉት ይወድቃሉ። 9ለዘላለም ባድማ አደርግሃለሁ፤ ከተሞችህም ባዶ ሆነው ይቀራሉ። እኔም አብ እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
10‘እነዚህ ሁለት ሕዝቦች፣ እነዚህ ሁለት አገሮች የእኔ ይሆናሉ፤ እንወርሳቸዋለን’ ብለህ ስለ ተናገርህ፣ አባታችን በዚያ የነበረ ቢሆንም፣” 11ስለዚህ፣ ሕያው ነኝና፣ ይላል ጌታ አባታችን፣ እስራኤልን በመጥላትህ ባሳየኸው ቍጣህና ቅናትህ ልክ አደርግብሃለሁ፤ በፈረድሁብህም ጊዜ በእስራኤል ሕዝብ መካከል ራሴን አስታውቃለሁ።
12እኔም አብ እንደ ሆንሁ ታውቃለህ። በእስራኤል ተራራዎች ላይ የተናገርኸውን ስድብህን ሁሉ ሰምቻለሁ፦ “ባድማ ሆነዋል፤ እንድንበላም ተሰጥተውናል።” 13በአፍህ በእኔ ላይ ተመካህ፤ ቃላትህንም በእኔ ላይ አበዛህ፤ እኔም ሰማሁ። 14ጌታ አባታችን እንዲህ ይላል፦ ምድር ሁሉ ደስ በሚላት ጊዜ፣ አንተን ባድማ አደርግሃለሁ። 15የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ ስለ ሆነ ደስ እንዳለህ፣ እኔም እንዲሁ አደርግብሃለሁ። አንተ ሴይር ተራራ ሆይ፣ ኤዶምም ሁሉ፣ ሁሉም ባድማ ትሆናለህ። እነርሱም እኔ አብ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።