የአባታችን ልጆች ተብለን መጠራታችን
አብ አሁን ልጆቹ ብሎ ይጠራቸዋል፤ ምን እንደሚሆኑ ግን ገና አልተገለጠም። ቃየን ማስጠንቀቂያ ነው፦ ጥላቻ ራሱ ነፍስ መግደል ነው። ፍቅር ክርስቶስ ሕይወቱን አሳልፎ መስጠቱ፣ ለተቸገረ ወንድምም እጅን መዘርጋት ነው። ልብ ሲፈርድብን አብ ይበልጣል።
3 1አባታችን የሰጠን ፍቅር ምን ዐይነት እንደ ሆነ እዩ፤ የአባታችን ልጆች ተብለን እንጠራለን! በእውነትም ነን። ዓለም እርሱን ስላላወቀ እኛን አያውቀንም። a a v1 የአባታችን ፍቅር ረቂቅ ሐሳብ አይደለም፤ የእርሱ ልጆች ያደርገናል፤ ይህም እውነተኛ ማንነታችን ነው። 2ወዳጆች ሆይ፣ አሁን የአባታችን ልጆች ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ነገር ግን እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ እርሱ እንዳለ ስለምናየው እንደ እርሱ እንሆናለን። 3በእርሱ ይህ ተስፋ ያለው ሁሉ፣ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።
4ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ ዐመፅንም ደግሞ ያደርጋል፤ ኀጢአት ዐመፅ ነው። 5እርሱ ኀጢአታችንን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፤ በእርሱም ኀጢአት የለም። 6በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኀጢአት አያደርግም፤ ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ አላየውም ወይም አላወቀውም።
7ልጆች ሆይ፣ ማንም አያስታችሁ። ጽድቅን የሚያደርግ፣ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጻድቅ ነው። 8ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ ከዲያብሎስ ነው፤ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ጀምሮ ኀጢአት ያደርጋልና። የአባታችን ልጅ የተገለጠበት ምክንያት የዲያብሎስን ሥራ ለማጥፋት ነው። 9ከአባታችን የተወለደ ማንም ኀጢአት አያደርግም፤ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከአባታችንም ስለ ተወለደ ኀጢአት ሊያደርግ አይችልም። 10የአባታችን ልጆች እነማን እንደ ሆኑ፣ የዲያብሎስም ልጆች እነማን እንደ ሆኑ የሚገልጠው ይህ ነው፤ ትክክል የሆነውን የማያደርግ ሁሉ ከአባታችን አይደለም፤ ወንድሙን ወይም እኅቱን የማይወድድም እንደዚሁ ነው።
እንደ ቤተ ሰብ እርስ በርስ መዋደድ
11ከመጀመሪያ የሰማችሁት መልእክት ይህ ነውና፤ እርስ በርስ እንድንዋደድ ነው። 12ከክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለ እንደ ቃየን አይደለም። ለምን ገደለው? የራሱ ሥራ ክፉ፣ የወንድሙ ሥራ ግን ጻድቅ ስለ ነበረ ነው። 13ወንድሞችና እኅቶች ሆይ፣ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። 14እርስ በርስ ስለምንዋደድ ከሞት ወደ ሕይወት እንዳለፍን እናውቃለን። የማይወድድ ሁሉ በሞት ይኖራል። 15ወንድሙን ወይም እኅቱን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በማንም ነፍሰ ገዳይ ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንደማይኖር ታውቃላችሁ።
16ፍቅርን የምናውቅበት ይህ ነው፤ ክርስቶስ ስለ እኛ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ፤ እኛም ደግሞ ሕይወታችንን እርስ በርስ አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል። 17ነገር ግን ማንም የዓለም ሀብት ያለው ሰው ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲቸገር አይቶ ልቡን ቢዘጋባቸው፣ የአባታችን ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል?
18ልጆች ሆይ፣ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ። 19ከእውነት እንደ መጣን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናረጋጋለን፤ 20ልባችን በሚኰንነን ጊዜ ሁሉ፤ አባታችን ከልባችን ይበልጣልና፤ ሁሉንም ያውቃል። 21ወዳጆች ሆይ፣ ልባችን ባይኰንነን በአባታችን ፊት ድፍረት አለን፤ 22ትእዛዛቱን ስለምንጠብቅ ደስ የሚያሰኘውንም ስለምናደርግ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እንቀበላለን። 23ትእዛዙም ይህ ነው፤ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናምን፣ እርሱም እንዳዘዘን እርስ በርስ እንድንዋደድ ነው። 24ትእዛዛቱን የሚጠብቅ ሁሉ በአባታችን ይኖራል፤ አባታችንም በእርሱ ይኖራል። በእኛ እንደሚኖር የምናውቅበት ይህ ነው፤ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ነው።