ካህናትና የተቀደሱ መሥዋዕቶች
ካህናት ርኩስ ሆነው ሳሉ ቅዱሱን ቍርባን መብላት የለባቸውም፤ ሊካፈሉት የሚችሉትም የገዛ ቤተ ሰባቸው ብቻ ናቸው። የሚቀርቡት እንስሳት ነውር የሌለባቸው መሆን አለባቸው፤ ዕውር፣ ጕንድሽ ወይም የተቀጠቀጠ አይሁን፤ ለአባታችን የሚሰጠው ያልፈለጋችሁትን የማስወገጃ መንገድ አይደለምና።
22 1አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤
2“አሮንንና ልጆቹን የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ የሚቀድሱትን የተቀደሱ መሥዋዕቶች በጥንቃቄ እንዲይዙ ንገራቸው፤ ይኸውም የተቀደሰውን ስሜን እንዳያረክሱ ነው። እኔ አባታችሁ ነኝ።
3“እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ከትውልድ እስከ ትውልድ ርኩስ ሆኖ ሳለ የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ ወደሚቀድሱት የተቀደሱ መሥዋዕቶች የሚቀርብ ከዘርህ ማንም ቢሆን፣ ከፊቴ ይወገዳል። እኔ አባታችሁ ነኝ።
4“ከአሮን ዘር የቈዳ በሽታ ወይም ፈሳሽ ያለበት ማንም ሰው እስኪነጻ ድረስ ከተቀደሱት መሥዋዕቶች አይብላ። ከሬሳ የሆነውን ርኩስ ነገር የሚነካ ማንም ሰው፣ ወይም የዘር ፈሳሽ የወጣበት ሰው፣ 5ወይም የሚያረክሰውን ተንቀሳቃሽ ፍጥረት የሚነካ፣ ወይም ርኩሰቱ ምንም ቢሆን የሚያረክሰውን ሰው የሚነካ፣ 6እንዲህ ያለውን የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ ሰውነቱንም በውሃ ካልታጠበ በቀር ከተቀደሱት መሥዋዕቶች አይብላ። 7ፀሐይ ስትጠልቅ ይነጻል፤ ከዚያም ከተቀደሱት መሥዋዕቶች ሊበላ ይችላል፤ ምግቡ ነውና። 8የሞተውን ወይም በአውሬ የተገደለውን ምንም ነገር አይብላ፤ ያ ያረክሰዋልና። እኔ አባታችሁ ነኝ። 9ካህናት ትእዛዜን ይጠብቁ፤ አለዚያ ንቀዋት በደለኛ ሆነው ይሞታሉ። የምቀድሳቸው አባታችሁ እኔ ነኝ።
10“ባዕድ ሰው ከተቀደሰው መሥዋዕት አይብላ፤ የካህኑ እንግዳ ወይም ተቀጣሪ ሠራተኛ አይብላው። 11ካህኑ ግን በገዛ ገንዘቡ ባሪያ ቢገዛ፣ ያ ባሪያ ሊበላው ይችላል፤ በካህኑ ቤት የተወለዱትም ከምግቡ ሊበሉ ይችላሉ። 12የካህን ልጅ ካህን ያልሆነን ሰው ብታገባ፣ ከተቀደሱት መባዎች አትብላ። 13የካህን ልጅ ግን ባሏ ሞቶባት ወይም ተፈትታ ልጅ ከሌላትና በወጣትነቷ ጊዜ እንደ ነበረች ወደ አባቷ ቤት ብትመለስ፣ ከአባቷ ምግብ ልትበላ ትችላለች። ባዕድ ሰው ግን አይብላው።
14“ማንም ስሕተት ሆኖበት የተቀደሰ መሥዋዕት ቢበላ፣ ከዋጋው አንድ አምስተኛ ጨምሮ ለካህኑ ይስጥ። 15ካህናት የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ የሚያቀርቡአቸውን የተቀደሱ መሥዋዕቶች አያርክሱ፤ 16የተቀደሱትን መሥዋዕቶቻቸውን በመብላት ካሳ የሚያስከፍል በደል በላያቸው አያምጡ። የምቀድሳቸው አባታችሁ እኔ ነኝና።”
ለአብ የሚገቡ መሥዋዕቶች
17አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤
18“አሮንን፣ ልጆቹንና እስራኤላውያንን ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ከእናንተ ማንም ቢሆን፣ የአገሩ ተወላጅም ይሁን በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ፣ ስእለት ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ የሚያቀርበው ስጦታ ሆኖ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእኔ ሲያቀርብ፣ 19ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ ከከብት፣ ከበግ ወይም ከፍየል ነውር የሌለበትን ተባዕት አቅርቡ። 20ነውር ያለበትን ምንም ነገር አታቅርቡ፤ ስለ እናንተ ተቀባይነት አያገኝምና። 21ማንም ልዩ ስእለት ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ የሚያቀርበው መሥዋዕት ሆኖ ከመንጋው ወይም ከከብቱ የኅብረት መሥዋዕት ለእኔ ሲያቀርብ፣ ተቀባይነት እንዲያገኝ ነውር የሌለበት ፍጹም መሆን አለበት፤ ምንም እንከን አይኑርበት። 22ዕውር፣ የተሰበረ፣ አካለ ጒዳተኛ፣ እባጭ ያለበት፣ ቅርፊት ያለው ወይም መግል የሚያዝረከርክ ምንም እንስሳ ለእኔ አታቅርቡ። ከእነዚህ አንዱን ስንኳ በመሠዊያው ላይ ለእኔ የምግብ መሥዋዕት አድርጋችሁ አታኑሩ። 23አካሉ የተበላሸ ወይም ያልጎለመሰ በሬ ወይም በግ በፈቃዳችሁ እንደ መሥዋዕት ልታቀርቡ ትችላላችሁ፤ ለስእለት ግን ተቀባይነት አያገኝም። 24ኰላላቱ የተቀጠቀጠ፣ የተፈጨ፣ የተቀደደ ወይም የተቈረጠ እንስሳ ለእኔ አታቅርቡ። በገዛ ምድራችሁ ይህን አታድርጉ። 25እንዲህ ያሉ እንስሳትን እንደ አባታችሁ ምግብ አድርጋችሁ ለማቅረብ ከመጻተኛ አትቀበሉ፤ አካላቸው የተበላሸና ነውር ያለባቸው ናቸውና፤ ስለ እናንተ ተቀባይነት አያገኙም።” a a v25 መሥዋዕቶቹ በምሳሌያዊ አነጋገር የእግዚአብሔር “ምግብ” ተብለው ተጠርተዋል፤ አባታችን ምንም አያስፈልገውም፣ ነገር ግን ስጦታው የሚገልጸውን አምልኮ ይቀበላል።
26አባታችንም ሙሴን እንዲህ አለው፤
27“ጥጃ፣ የበግ ጠቦት ወይም ፍየል በተወለደ ጊዜ፣ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋራ ይቈያል፤ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ለእኔ እንደ ምግብ መሥዋዕት ተቀባይነት አለው። 28ላም ወይም በግ ከግልገሉ ጋራ በአንድ ቀን አትረዱ።
29“ለእኔ የምስጋና መሥዋዕት በምትሠዉበት ጊዜ፣ ተቀባይነት እንድታገኙ አድርጋችሁ ሠዉት። 30በዚያው ቀን ይበላ፤ እስከ ጥዋት ድረስ ከእርሱ ምንም አታስቀሩ። እኔ አባታችሁ ነኝ።
31“ትእዛዜን ጠብቁ፤ ፈጽሙአቸውም። እኔ አባታችሁ ነኝ። 32የተቀደሰውን ስሜን አታርክሱ፤ በእስራኤላውያን መካከል እንደ ቅዱስ ልከበር ይገባል። የምቀድሳችሁ አባታችሁ እኔ ነኝ፤ 33አባታችሁም ለመሆን ከግብፅ ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ። እኔ አባታችሁ ነኝ።”