አባታችን ኢያሱን ሾመ
በኢያሱ መሪነት የተስፋይቱ ምድር መወረስና መሰፈር። አስፈሪ ሥራ ሲጀመር፣ አብ ሕዝቡን በራሳቸው ድፍረት ሳይሆን በእርሱ መገኘት ያጸናቸዋል።
1 1የአባታችን አገልጋይ ሙሴ ከሞተ በኋላ፣ አባታችን የሙሴን ረዳት የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ አለው፤
2“አገልጋዬ ሙሴ ሞቷል። አሁን ተነሥተህ አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ለእነርሱ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ግቡ። 3ሙሴን ተስፋ እንደ ሰጠሁት፣ እግርህ የሚረግጠውን ስፍራ ሁሉ ለአንተ ሰጥቻለሁ። 4ድንበርህ ከምድረ በዳውና ከዚህ ሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ፣ የኬጢያውያንም ምድር ሁሉ፣ እስከ ታላቁ ባሕር እስከ ፀሓይ መግቢያ ድረስ ይደርሳል። 5በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ማንም ሊቆምብህ አይችልም። ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ፣ ከአንተም ጋር እሆናለሁ፤ አልተውህም፤ አልጥልህም።
6“በርታ፤ ጠንካራም ሁን፤ ለአባቶቻቸው ልሰጣቸው የማልሁላትን ምድር እንዲወርሱ ይህን ሕዝብ ትመራቸዋለህና። 7ብቻ በርታ፤ እጅግም ጠንካራ ሁን፤ አገልጋዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ለመጠበቅ ተጠንቀቅ። በሄድህበት ሁሉ እንድትከናወንልህ፣ ከእርሱ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ አትበል። 8ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ ከቶ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ ታደርግ ዘንድ፣ ቀንና ሌሊት አሰላስለው። ያን ጊዜ መንገድህ ይቀናል፤ ይከናወንልሃል። 9አላዘዝሁህምን? በርታ፤ ጠንካራም ሁን። አትፍራ፤ አትደንግጥ፤ እኔ አባትህ በሄድህበት ሁሉ ከአንተ ጋር ነኝና።”
ኢያሱ ሕዝቡን ለመሻገር አነሣሣ
10ከዚያም ኢያሱ የሕዝቡን አለቆች እንዲህ አዘዛቸው፤
11“በሰፈሩ ውስጥ ዙሩና ሕዝቡን እንዲህ እዘዙ፤ ‘ስንቅ አዘጋጁ፤ አባታችሁ ትወርሷት ዘንድ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ለመያዝ፣ ከሦስት ቀን በኋላ ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁና።’”
12ኢያሱም ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ እንዲህ አለ፤
13“የአባታችን አገልጋይ ሙሴ ያዘዛችሁን ቃል አስታውሱ፤ ‘አባታችሁ ዕረፍት ይሰጣችኋል፤ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል።’ 14ሚስቶቻችሁ፣ ልጆቻችሁና ከብቶቻችሁ ሙሴ በዮርዳኖስ ምሥራቅ በሰጣችሁ ምድር ይቅሩ፤ እናንተ ተዋጊዎች ሁሉ ግን ወንድሞቻችሁን ልትረዱ ከፊታቸው ታጥቃችሁ ተሻገሩ፤ 15አባታችን ለእናንተ እንደ ሰጣችሁ ለወንድሞቻችሁም ዕረፍት እስኪሰጥ፣ እነርሱም እርሱ የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፣ ከዚያም ወደ ገዛ ምድራችሁ ተመልሳችሁ ውረሷት፤ ይህችም የአባታችን አገልጋይ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በፀሓይ መውጫ በኩል የሰጣችሁ ምድር ናት።”
16እነርሱም ኢያሱን መልሰው እንዲህ አሉት፤ “ያዘዝኸንን ሁሉ እናደርጋለን፤ ወደ ላክኸንም ስፍራ ሁሉ እንሄዳለን። 17በሁሉ ነገር ሙሴን እንደ ታዘዝነው፣ አንተንም እንታዘዝሃለን። ብቻ አባትህ ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ፣ ከአንተም ጋር ይሁን። 18ትእዛዝህን የሚቃወም፣ የምታዝዘውንም ሁሉ ቃልህን የማይታዘዝ ማንም ሰው ይገደል። አንተ ብቻ በርታ፤ ጠንካራም ሁን።”