ሙሴ በተራራው ላይ
ሙሴ ናባው ተራራ ይወጣል፤ አብም የማይገባባትን ምድር ሁሉ ያሳየዋል። በመቶ ሃያ ዓመቱ ዓይኑ ሳይፈዝ በዚያ ይሞታል፤ አብም ማንም በማያውቀው ስፍራ ይቀብረዋል። እስራኤል ሠላሳ ቀን ያለቅሳሉ። ከዚያ ወዲህ አብ ፊት ለፊት ያወቀው እንደ እርሱ ያለ ነቢይ አልተነሣም።
34 1ሙሴም ከሞዓብ ሜዳ ተነሥቶ ኢያሪኮን ወደሚመለከተው ወደ ናባው ተራራ፣ ወደ ጲስጋ ጫፍ ወጣ፤ አባታችንም ምድሪቱን ሁሉ አሳየው፦ ከገለዓድ እስከ ዳን፣ 2ንፍታሌምን ሁሉ፣ የኤፍሬምንና የምናሴን ምድር፣ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ የይሁዳን ምድር ሁሉ፣ 3ኔጌብን፣ ሜዳውንም፦ የዘንባባ ከተማ የሆነችውን የኢያሪኮን ሸለቆ፣ እስከ ዞዓር አሳየው።
4አባታችንም እንዲህ አለው፤ “‘ለዘርህ እሰጣታለሁ’ ብዬ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የማልኩላት ምድር ይህች ናት። በዐይንህ እንድታያት አድርጌአለሁ፤ ነገር ግን ወደ እርስዋ አትሻገርም።”
5የአባታችን አገልጋይ ሙሴም አባታችን እንዳለው በሞዓብ ምድር በዚያ ሞተ። 6አባታችንም ቤትፌጎርን በሚያስተያየው በሞዓብ ሸለቆ ቀበረው፤ የመቃብሩን ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የሚያውቅ የለም። 7ሙሴ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ዓመት ነበር፤ ዐይኖቹ አልፈዘዙም፣ ጕልበቱም አልጠፋም። 8የእስራኤል ልጆችም የልቅሶውና የሐዘኑ ቀኖች እስኪፈጸሙ ድረስ ሙሴን በሞዓብ ሜዳ ሠላሳ ቀን አለቀሱለት። 9ሙሴ እጆቹን ጭኖበት ስለ ነበር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብ መንፈስ ሞልቶበት ነበር። የእስራኤልም ልጆች ሰሙት፣ አባታችን ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 10ከዚያም ወዲህ አባታችን ፊት ለፊት እንደ ዐወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ በእስራኤል አልተነሣም፤ 11ይህም አባታችን በግብፅ፣ በፈርዖንና በሎሌዎቹ ሁሉ፣ በምድሩም ሁሉ ላይ እንዲያደርግ ስለ ላከው ስለ ምልክቶቹና ስለ ድንቆቹ ሁሉ ነው፤ 12ሙሴም በእስራኤል ሁሉ ዐይን ፊት ስላደረገው ስለ ብርቱ እጁ ሁሉ፣ ስለ ታላቁም የሚያስፈራ ሥራ ሁሉ ነው።