ቅረቡ፣ አሕዛብ ሁሉ
አሕዛብ አስፈሪ ነገር እንዲሰሙ ተጠርተዋል፤ የአብ ሰይፍ በኤዶም ጠግቧል፤ በተራሮች ላይ ደም አለ፤ ወንዞች ወደ ዝፍት ተለውጠዋል፤ ጢሱም ሳያቋርጥ ይወጣል። ጉጉቶችና ቀበሮዎች በሁከት ገመድ የተለካውን ፍርስራሽ ይወርሳሉ። ምንም እፎይታ አይሰጥም፤ ለጽዮን የሚሆን ፍትሕ ብቻ ነው።
34 1እናንተ አሕዛብ ሆይ፣ ቅረቡና አድምጡ፤ እናንተ ሕዝቦች ሆይ፣ አድምጡ! ምድርና በውስጧ የሞላው ሁሉ፣ ዓለሙና የሚያወጣው ሁሉ ይስሙ። 2አባታችን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቍጣ ተሞልቶአልና፤ መዓቱም በሰራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው። ለጥፋት ለይቶአቸዋል፤ ለእርድም አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል። 3የተገደሉት ይጣላሉ፤ የሬሳዎቻቸው ክርፋት ይወጣል፤ ተራሮችም በደማቸው ይቀልጣሉ። 4የሰማይ ከዋክብት ሁሉ ይበሰብሳሉ፤ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ይጠቀለላሉ። የከዋክብቱ ሰራዊት ሁሉ፣ ቅጠል ከወይን ተክል ረግፎ እንደሚጠወልግ ይጠወልጋሉ፤ ከበለስ ዛፍ እንደሚረግፍ የኰመሰሰ በለስ።
5ሰይፌ በሰማያት ከጠገበ በኋላ፣ እነሆ፣ በኤዶም ላይ ለፍርድ ይወርዳል፤ ለጥፋት በለየኋቸው ሕዝብ ላይ። 6አባታችን ሰይፍ አለው፤ በደም ጠግቦአል፤ በስብም ተሞልቶአል፤ በጠቦቶችና በፍየሎች ደም፣ በአውራ በጎች ኵላሊት ስብ። አባታችን በባሶራ መሥዋዕት፣ በኤዶም ምድር ታላቅ እርድ አለውና። 7የዱር በሬዎች ከእነርሱ ጋር ይወድቃሉ፤ ወይፈኖችም ከኀያላኑ ጋር። ምድራቸው በደም ትጠግባለች፤ አፈራቸውም በስብ ይሞላል። 8አባታችን የፍርድ ቀን፣ ለጽዮንም ጉዳይ የበቀል ዓመት አለውና። 9የኤዶም ወንዞች ወደ ዝፍት፣ አፈሯም ወደ ዲን ይለወጣሉ፤ ምድሯም የሚነድድ ዝፍት ትሆናለች። 10ሌሊትና ቀን አይጠፋም፤ ጢሱም ለዘላለም ይወጣል። ከትውልድ እስከ ትውልድ ባድማ ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ለዘላለም ማንም አያልፍባትም። 11የበረሓ ጕጕትና ጩኸታም ጕጕት ይወርሷታል፤ ታላቁ ጕጕትና ቍራ በውስጧ ያድራሉ። አባታችን የሁከትን መለኪያ ገመድ፣ የባዶነትንም የሚዛን ገመድ ይዘረጋባታል። 12መኳንንቶቿ መንግሥት ብለው የሚጠሩት በዚያ አይኖራቸውም፤ አለቆቿም ሁሉ ከንቱ ይሆናሉ። 13እሾህ ምሽጎቿን፣ ኵርንችትና አሜከላም አምባዎቿን ይወርሳሉ። የቀበሮዎች ማደሪያ፣ የሰጎኖችም መኖሪያ ትሆናለች። 14የምድረ በዳ አራዊት ከጅቦች ጋር ይገናኛሉ፤ የዱር ፍየሎችም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ በዚያም የሌሊቱ ፍጡር ይሰፍራል፤ ለራሱም ማረፊያ ስፍራ ያገኛል። 15በዚያ ጕጕት ጎጆ ትሠራለች፤ እንቍላሎቿን ትጥላለች፤ ትፈለፍላቸዋለች፤ ጫጩቶቿንም ከጥላዋ በታች ትሰበስባለች፤ በዚያም ጭልፊቶች፣ እያንዳንዷ ከጓደኛዋ ጋር ይሰበሰባሉ።
16የአባታችንን መጽሐፍ ፈልጉና አንብቡ፤ ከእነዚህ አንዱም አይጠፋም፤ አንዷም ጓደኛዋን አታጣም። አፉ አዝዞአልና፤ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋል። 17ዕጣ ጣለላቸው፤ እጁም ድርሻቸውን በገመድ ለካላቸው። ለዘላለም ይወርሷታል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም በዚያ ያድራሉ።