ኖኅ ወደ መርከቡ ገባ
መጠበቁ ያበቃል። የኖኅ ቤተሰብና እንስሳቱ ይገባሉ፤ አብ በሩን ይዘጋል፤ ውኃም ከታችና ከላይ አርባ ቀን ይመጣል። ምዕራፉ የሞቱትን በግልጽ ይቆጥራል፤ በየብስ ላይ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ፤ አንዲት መርከብ ግን ትንሳፈፋለች።
7 1አባታችንም ኖኅን እንዲህ አለው፤ “አንተና ቤተ ሰብህ ሁሉ ወደ መርከቡ ግቡ፤ በዚህ ትውልድ መካከል በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና። 2ከንጹሕ እንስሳ ሁሉ ተባትና እንስት አድርገህ ሰባት ሰባት ጥንድ፣ ንጹሕ ካልሆነው እንስሳ ደግሞ ተባትና እንስት አንድ ጥንድ ለአንተ ውሰድ፤ 3ከሰማይ ወፎችም ደግሞ ተባትና እንስት ሰባት ሰባት ጥንድ ውሰድ፤ ይህም በምድር ሁሉ ላይ ዘርን ለማቆየት ነው። 4ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁና፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ነገር ሁሉ ከምድር ፊት አጠፋለሁ።”
5ኖኅም አባታችን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
6የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በመጣ ጊዜ ኖኅ የስድስት መቶ ዓመት ሰው ነበር። 7እርሱም ከወንዶች ልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ከጥፋት ውኃ ለማምለጥ ወደ መርከቡ ገባ። 8ከንጹሕ እንስሳትና ንጹሕ ካልሆኑ እንስሳት፣ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡት ሁሉ፣ 9አባታችን ኖኅን እንዳዘዘው ተባትና እንስት ሁለት ሁለት ሆነው ወደ ኖኅ ወደ መርከቡ መጡ። 10ከሰባቱ ቀን በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ መጣ። 11ኖኅ በስድስት መቶኛ ዓመቱ፣ በሁለተኛው ወር፣ በወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን፣ በዚያኑ ዕለት የታላቁ ጥልቅ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፤ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ። 12ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዘነበ።
13በዚያኑ ዕለት ኖኅ፣ እርሱም ከወንዶች ልጆቹ ከሴም ከካምና ከያፌት፣ ከሚስቱና ከሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ጋር ወደ መርከቡ ገባ። 14እነርሱም ዱር አራዊት ሁሉ እንደ ወገኑ፣ የቤት እንስሳ ሁሉ እንደ ወገኑ፣ በምድር ላይ የሚሳብ ሁሉ እንደ ወገኑ፣ ወፍ ሁሉ እንደ ወገኑ፣ ክንፍ ያለው ፍጡር ሁሉ፤ 15የሕይወት እስትንፋስ ያለው ሥጋ ሁሉ ሁለት ሁለት ሆነው ወደ ኖኅ ወደ መርከቡ መጡ። 16አባታችን እንዳዘዘው ከሥጋ ሁሉ ተባትና እንስት ገቡ፤ ከዚያም አባታችን በሩን ዘጋበት። 17የጥፋት ውኃውም አርባ ቀን በምድር ላይ ቈየ፤ ውኃውም በረከተ መርከቡንም አነሣው፤ ከምድርም በላይ ከፍ ከፍ አለ። 18ውኃውም እጅግ ጐልብቶ በምድር ላይ በዛ፤ መርከቡም በውኃው ላይ ተንሳፈፈ። 19ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም ጐልብቶ በሰማይ ሁሉ ሥር ያሉት ረጃጅም ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ። 20ውኃውም ተራሮቹን ሸፍኖ ከእነርሱ በላይ ሃያ ሁለት ጫማ ያህል ከፍ ብሎ ወጣ። 21በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ ሁሉ ማለት ወፎች፣ የቤት እንስሳት፣ ዱር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚራቡ ፍጡራን ሁሉ፣ ሰዎችም ሁሉ ሞቱ። 22በየብስ ላይ ካለው ሁሉ በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስ የነበረው ሁሉ ሞተ። 23አባታችንም በምድር ፊት ላይ የነበረውን ሕያው ነገር ሁሉ፣ ሰዎችን፣ እንስሳትን፣ የሚሳቡ ፍጡራንንና የሰማይ ወፎችን አጠፋ፤ ከምድርም ጠራረጋቸው። ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከብ ውስጥ የነበሩት ብቻ ቀሩ። 24ውኃውም መቶ ኀምሳ ቀን በምድር ላይ ጸንቶ ቈየ።