ከእሳት በቀር ለምንም የማይጠቅም ወይን
አጭርና ጨለምተኛ ምስል። የወይን ግንድ እንጨት ሳይቃጠል እንኳ ለሥራ አይጠቅምም፤ ከከሰለ ደግሞ እጥፍ አይጠቅምም። አብ እንደሚለው የኢየሩሳሌም ሕዝብ ለእርሱ እንዲሁ ናቸው፦ ለእሳት የተጠበቁ፣ ለምንም ሥራ የማይበቁ።
15 1ከዚያም የአባታችን ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
2“የሰው ልጅ ሆይ፣ በዱር ዛፎች መካከል ያለው የወይን ቅርንጫፍ፣ የወይኑ እንጨት ከማንኛውም እንጨት እንዴት ይበልጣል? 3እንጨቱ ለጠቃሚ ነገር ይውላልን? ነገር ለመስቀል ከእርሱ ችካል ይሠራልን? 4እነሆ፣ ለማገዶ ወደ እሳት ይጣላል። እሳቱ ሁለቱን ጫፎች ይበላል፤ መካከሉም ይቃጠላል። ለማንኛውም ሥራ ይጠቅማልን? 5ሙሉ ሆኖ ሳለ የማይጠቅም ከሆነ፣ እሳት ከበላውና ከተቃጠለ በኋላማ እንዴት ይበልጥ አይጠቅም! ለአንዳች ነገር ሊውል ይችላልን?”
6ስለዚህ ጌታ አባታችን እንዲህ ይላል፤ “በዱር ዛፎች መካከል ያለውን የወይን እንጨት ለማገዶ ለእሳት እንደ ሰጠሁ፣ እንዲሁ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳልፌ ሰጠኋቸው። 7ፊቴን በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ። ከአንዱ እሳት አመለጡ፣ ሌላው ግን ይበላቸዋል፤ ፊቴን በእነርሱ ላይ ባደረግሁ ጊዜ፣ እኔ አባታችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8ፈጽመው ታማኝ ባለመሆናቸው ምክንያት፣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፣ ይላል ጌታ አባታችን።”