የጌታ ቀን ይመጣል
ቀኑ እንደ ሌባ ይመጣል፤ እነርሱ ግን ስለ እርሱ በጨለማ ውስጥ አይደሉም፤ ስለዚህ ንቁ፤ በልባምነትም ኑሩ። መደምደሚያው ፈጣን ዝርዝር ነው፤ መሪዎቻችሁን አክብሩ፣ ተስፋ የቈረጡትን አጽናኑ፣ ታገሡ፣ ደስ ይበላችሁ፣ ጸልዩ፣ አመስግኑ፣ ሁሉን ፈትኑ፣ መልካሙንም ያዙ።
5 1ወንድሞችና እኀቶች ሆይ፤ ስለ ዘመናትና ስለ ወቅቶች የሚጻፍላችሁ ነገር አያስፈልጋችሁም። 2የጌታችን የኢየሱስ ቀን ሌሊት እንደሚመጣ ሌባ እንደሚመጣ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ። 3ሰዎች፣ “ሰላምና ደኅንነት” ባሉ ጊዜ፣ ፅንስ እንደያዘች ሴት ምጥ፣ ድንገተኛ ጥፋት ይደርስባቸዋል፤ ከቶም አያመልጡም። 4እናንተ ግን ወንድሞችና እኀቶች ሆይ፤ ያ ቀን እንደ ሌባ ድንገት እንዲደርስባችሁ በጨለማ ውስጥ አይደላችሁም። 5እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆችና የቀን ልጆች ናችሁ፤ እኛ የሌሊትም ሆነ የጨለማ አይደለንም። 6እንግዲህ እንደ ሌሎች አንተኛ፤ ነገር ግን ነቅተንና ነጥረን እንኑር። 7የሚተኙ ሌሊት ይተኛሉና፤ የሚሰክሩም ሌሊት ይሰክራሉ። 8እኛ ግን የቀን ስለ ሆንን፣ እምነትንና ፍቅርን እንደ ጥሩር፣ የድነትን ተስፋ እንደ ራስ ቍር ለብሰን እንንቃ። 9አባታችን ለቍጣ አልመደበንም፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድነትን እንድናገኝ ነው እንጂ፤ 10እርሱም ነቅተንም ሆነ ተኝተን ከእርሱ ጋራ አብረን በሕይወት እንድንኖር ስለ እኛ ሞተ። 11ስለዚህ አሁን እንደምታደርጉት እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ፤ አንዳችሁም ሌላውን ገንቡ።
እንደ ብርሃን ልጆች መኖር
12ወንድሞችና እኀቶች ሆይ፤ በመካከላችሁ የሚደክሙትን፣ በጌታ የሚመሯችሁንና የሚገሥጿችሁን እንድታከብሩ እንለምናችኋለን። 13ስለ ሥራቸው በፍቅር እጅግ ከፍ አድርጋችሁ አክብሯቸው። እርስ በርሳችሁም በሰላም ኑሩ።
14ወንድሞችና እኀቶች ሆይ፤ የማይሠሩትን እንድትገሥጹ፣ የተስፋ ቍርጥ የሆኑትን እንድታጽናኑ፣ ደካሞችን እንድትደግፉ፣ ለሁሉም እንድትታገሡ እናሳስባችኋለን። 15ማንም ለማንም ክፉን በክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁና ለሁሉም መልካሙን ተከታተሉ።
16ዘወትር ደስ ይበላችሁ፤ 17ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ 18በሁሉም ነገር አመስግኑ፤ ይህ ለእናንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የአባታችን ፈቃድ ነውና። 19መንፈስ ቅዱስን አታጥፉ። 20ትንቢቶችን አትናቁ፤ 21ነገር ግን ሁሉን መርምሩ፤ መልካሙን ያዙ። 22ከክፋት ዐይነት ሁሉ ራቁ።
23የሰላም አባታችን ራሱ ፈጽሞ ይቀድሳችሁ፤ መንፈሳችሁና ነፍሳችሁ ሥጋችሁም ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ነቀፋ የሌለበት ሆኖ ይጠበቅ። 24የሚጠራችሁ ታማኝ ነው፤ እርሱም ይህን በእርግጥ ይፈጽማል።
25ወንድሞችና እኀቶች ሆይ፤ ስለ እኛ ጸልዩ።
26ወንድሞችንና እኀቶችን ሁሉ በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ስጡ። 27ይህች መልእክት ለወንድሞችና ለእኀቶች ሁሉ እንድትነበብ በጌታ ፊት አዛችኋለሁ።
28የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን።