ለአብ ፈቃድ የታጠቀ
ከእነርሱ ጋር መተባበር ስታቆሙ የቀድሞ ወዳጆቻችሁ ይከፋቸዋል፤ ጴጥሮስም ይህን ጠብቁ ይላል። አንባቢዎቹ አእምሮአቸው የነቃ እንዲሆን፣ ሳያጕረመርሙ እንግዳ እንዲቀበሉና ያላቸውን ማንኛውንም ስጦታ እንዲጠቀሙ ይነግራቸዋል። የእሳት ፈተና እንግዳ ነገር አይደለም፤ ፍርድ የሚጀምረው ከአባታችን ቤተሰብ ነው።
4 1እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋ መከራ ስለተቀበለ፣ እናንተም በዚሁ አሳብ ታጠቁ፤ በሥጋ መከራ የተቀበለ ከኀጢአት ተለይቷልና። 2ስለዚህ ከእንግዲህ የቀረውን ዘመን በሥጋ ሳላችሁ ለሰው ምኞት ሳይሆን ለአባታችን ፈቃድ ኑሩ። 3አብን የማያውቁ ሰዎች የሚፈልጉትን ስታደርጉ ያሳለፋችሁት ዘመን ይበቃል፤ በመዳራት፣ በክፉ ምኞት፣ በስካር፣ በዘፈናማ ግብዣ፣ በመጠጥ ዝንፍያና በዓመፀኛ ጣዖት አምልኮ ኖራችኋል። 4ከእንግዲህ ከእነርሱ ጋር ወደዚያው የመዳራት ጎርፍ ስለማትሮጡ ይደነቃሉ፤ ስለዚህ ይሰድቧችኋል። 5እነርሱ ግን በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ተዘጋጅቶ ላለው መልስ ይሰጣሉ። 6ወንጌል አሁን ለሞቱትም የተሰበከበት ምክንያት ይህ ነው፤ እንደ ሰው ሁሉ በሥጋ ይፈረድባቸው ዘንድ፣ ነገር ግን እንደ አባታችን በመንፈስ ይኖሩ ዘንድ ነው።
7የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ ትጸልዩ ዘንድ ልባሞችና ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ። 8ከሁሉም በላይ እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ ፍቅር የኀጢአትን ብዛት ይሸፍናልና። 9ያለ ማጉረምረም እርስ በርሳችሁ እንግዳ ተቀባዮች ሁኑ። 10እያንዳንዳችሁ የተለያየውን የአባታችንን ጸጋ እንደሚያስተዳድሩ መልካም መጋቢዎች፣ የተቀበላችሁትን ስጦታ ሌሎችን ለማገልገል ተጠቀሙበት። 11የሚናገር ቢኖር የአባታችንን ቃል እንደሚያስተላልፍ ሆኖ ይናገር፤ የሚያገለግል ቢኖር እርሱ በሚሰጠው ኀይል ያገልግል፤ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሁሉ ነገር እርሱ እንዲከብር ነው። ክብርና ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን። አሜን።
በአብ ስም መከራ መቀበል
12ወዳጆች ሆይ፤ የሚፈትናችሁ የእሳት መከራ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ አድርጋችሁ አትደነቁ። 13ነገር ግን የክርስቶስን መከራ በተካፈላችሁ መጠን ደስ ይበላችሁ፤ ክብሩ ሲገለጥ በታላቅ ሐሤት ደስ እንዲላችሁ ነው። 14ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ ብፁዓን ናችሁ፤ የክብርና የአባታችን መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና። 15ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ ወይም በሌሎች ጒዳይ ጣልቃ ገብ ሆኖ መከራ አይቀበል። 16ክርስቲያን ሆናችሁ መከራ ብትቀበሉ ግን አትፈሩ፤ ነገር ግን ያን ስም ስለተሸከማችሁ አባታችንን አመስግኑ። 17ፍርድ ከአባታችን ቤተ ሰብ የሚጀምርበት ጊዜ ነውና፤ ከእኛ ቢጀምር፣ የአባታችንን ወንጌል የማይታዘዙትን ምን ይጠብቃቸዋል? 18ደግሞም፣ “ጻድቅ እንኳ በጭንቅ የሚድን ከሆነ፣ ዓመፀኛውና ኀጢአተኛው ምን ይሆናሉ?” 19እንግዲህ በአባታችን ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ መልካም እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነው ፈጣሪ ያደራ ይስጡ።