ከዋናው እረኛ በታች ያሉ እረኞች
ሽማግሌዎች የአባታችንን መንጋ ለገንዘብ ሳይሆን፣ በማንም ላይ ሳይሠለጥኑ በፈቃደኝነት እንዲጠብቁ ታዘዙ። ሌሎቹ ሁሉ ትሕትናን እንዲለብሱና ጭንቀታቸውን ለሚያስብላቸው ለአባታችን እንዲጥሉ ታዘዙ። ዲያብሎስ ይዞራል፤ መከራው ግን አጭርና በዓለም ሁሉ ያለ ነው።
5 1በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች፣ ባልንጀራ ሽማግሌ እንደ መሆኔ፣ የክርስቶስን መከራ ምስክር እንደ መሆኔ፣ ሊገለጥ ባለው ክብር ተካፋይ እንደ መሆኔ እማልዳቸዋለሁ፤ 2በመካከላችሁ ያለውን የአባታችንን መንጋ ጠብቁት፤ አባታችን እንደሚወድደው በግዴታ ሳይሆን በውዴታ፣ በሚያሳፍር ረብ ሳይሆን በትጋት እየጠበቃችሁት፤ 3ለእናንተ በአደራ የተሰጧችሁን በመግዛት ሳይሆን፣ ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁት። 4ዋናው እረኛ በሚገለጥበትም ጊዜ የማይጠፋውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ። a a v4 ዋናው እረኛ ኢየሱስ ነው፤ ታማኝ ሽማግሌዎች ከእርሱ በታች የሚያገለግሉት፣ በሚገለጥበትም ጊዜ የሚከፍላቸው እርሱ ነው።
5እንዲሁም እናንተ ታናናሾች ለሽማግሌዎች ተገዙ። ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ ትሕትናን ልበሱ፤ አባታችን ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 6እንግዲህ በተገቢው ጊዜ ከፍ ከፍ እንዲያደርጋችሁ፣ ከአባታችን ኀያል እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ 7እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና ጭንቀታችሁን ሁሉ በአባታችን ላይ ጣሉ።
8በመጠን ኑሩ፤ ንቁ፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራል። 9በዓለም ያሉ ወንድሞቻችሁ ያንኑ መከራ እንደሚቀበሉ እያወቃችሁ፣ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
10በክርስቶስ ወደ ዘላለማዊ ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አባታችን፣ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ፣ እርሱ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል፣ ያጸናችኋል፣ ያበረታችኋል፣ መሠረትም ይጥልላችኋል። 11ለእርሱ ለዘላለም ግዛት ይሁን። አሜን።
12እኔ እንደማስበው ታማኝ ወንድም በሆነው በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጻፍሁላችሁ፤ ይህም የአባታችን እውነተኛ ጸጋ መሆኑን እየመሰከርሁ አበረታታኋችሁ። በእርሱ ጽኑ።
የመጨረሻ ሰላምታ
13ከእናንተ ጋር አብራ የተመረጠችው በባቢሎን ያለችው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም እንዲሁ። b b v13 እዚህ ላይ “ባቢሎን” ለጥንቷ ከተማ ሳይሆን፣ ጴጥሮስ የጻፈባት የግዛት ማዕከል ለሆነችው ለሮም የተሰወረ ስም ሳይሆን አይቀርም። 14እርስ በርሳችሁ በፍቅር መሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን።