የመለከት በዓል
ሰባተኛው ወር የተሞላ ነው፤ የመለከት ድምፅ፣ የስርየት ቀን ራስን ማዋረድ፣ ከዚያም የዳስ በዓል፤ በዚያም ወይፈኖቹ በሰባት ቀናት ውስጥ ከዐሥራ ሦስት ወደ ሰባት ይቀንሳሉ፤ በመጨረሻም የመዝጊያ ጉባኤ ይሆናል። እያንዳንዱ በዓል ትክክለኛ ቍርባኑ አለው፤ ሁልጊዜም ከዕለታዊው ጋር።
29 1“በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የተለመደውን ሥራ ምንም አትሥሩ፤ መለከት የምትነፉበት ቀን ነውና። 2ለአባታችን መልካም መዐዛ የሚሆን የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ የአንድ ዓመት ሰባት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይሁኑ። 3በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የእህል ቍርባናቸው ይሁን፤ ለወይፈኑ ስድስት ሊትር ያህል፣ ለአውራ በጉ አራት ሊትር ያህል፣ 4ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሊትር ያህል፤ 5ስለ እናንተም ማስተስረያ ለማድረግ አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ። 6ይህም ከመባቻው የሚቃጠል መሥዋዕትና ከእህል ቍርባኑ፣ ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕትና ከእህል ቍርባኑ፣ እንደ ሥርዐታቸውም ከመጠጥ ቍርባናቸው በተጨማሪ ነው፤ ይህም ለአባታችን የሚያረካ መዐዛ፣ በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።
የማስተስረያ ቀን
7“በዚህ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን የተቀደሰ ስብሰባ አድርጉ፤ ራሳችሁንም አስጨንቁ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ። 8ለአባታችን መልካም መዐዛ የሚሆን የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ የአንድ ዓመት ሰባት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይሁኑ። 9በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የእህል ቍርባናቸው ይሁን፤ ለወይፈኑ ስድስት ሊትር ያህል፣ ለአንዱ አውራ በግ አራት ሊትር ያህል፣ 10ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሊትር ያህል፤ 11ደግሞም አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም ከማስተስረያው የኀጢአት መሥዋዕት፣ ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕትና ከእህል ቍርባኑ፣ ከመጠጥ ቍርባናቸውም በተጨማሪ ነው።
የዳስ በዓል
12“በሰባተኛው ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የተለመደውን ሥራ ምንም አትሥሩ፤ ለአባታችንም ሰባት ቀን በዓልን አክብሩ። 13ለአባታችን መልካም መዐዛ የሚሆን በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ ዐሥራ ሦስት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎች፣ የአንድ ዓመት ዐሥራ አራት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይሁኑ። 14በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የእህል ቍርባናቸው ይሁን፤ ለዐሥራ ሦስቱ ወይፈኖች ለእያንዳንዳቸው ስድስት ሊትር ያህል፣ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዳቸው አራት ሊትር ያህል፣ 15ለዐሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሊትር ያህል፤ 16አንድ አውራ ፍየልም የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባኑ በተጨማሪ ነው።
17“በሁለተኛው ቀን ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎች፣ የአንድ ዓመት ዐሥራ አራት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይቅረቡ፤ 18ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለጠቦቶቹ እንደ ቍጥራቸው፣ እንደ ተወሰነውም የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርቡ፤ 19ደግሞም አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባናቸው በተጨማሪ ነው።
20“በሦስተኛው ቀን ዐሥራ አንድ ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎች፣ የአንድ ዓመት ዐሥራ አራት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይቅረቡ፤ 21ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለጠቦቶቹ እንደ ቍጥራቸው፣ እንደ ተወሰነውም የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርቡ። 22ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕት ከእህልና ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በተጨማሪ አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።
23“በአራተኛው ቀን ዐሥር ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎች፣ የአንድ ዓመት ዐሥራ አራት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይቅረቡ፤ 24ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለጠቦቶቹ እንደ ቍጥራቸው፣ እንደ ተወሰነውም የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርቡ፤ 25ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕት ከእህልና ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በተጨማሪ አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።
26“በአምስተኛው ቀን ዘጠኝ ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎች፣ የአንድ ዓመት ዐሥራ አራት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይቅረቡ፤ 27ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለጠቦቶቹ እንደ ቍጥራቸው፣ እንደ ተወሰነውም የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርቡ። 28ደግሞም አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባኑ በተጨማሪ ነው።
29“በስድስተኛው ቀን ስምንት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎች፣ የአንድ ዓመት ዐሥራ አራት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይቅረቡ፤ 30ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለጠቦቶቹ እንደ ቍጥራቸው፣ እንደ ተወሰነውም የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርቡ፤ 31አንድ አውራ ፍየልም የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባናቸው በተጨማሪ ነው።
32“በሰባተኛው ቀን ሰባት ወይፈኖች፣ ሁለት አውራ በጎች፣ የአንድ ዓመት ዐሥራ አራት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይቅረቡ፤ 33ለወይፈኖቹ፣ ለአውራ በጎቹና ለጠቦቶቹ እንደ ቍጥራቸው፣ እንደ ተደነገገውም የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርቡ፤ 34አንድ አውራ ፍየልም የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባኑ በተጨማሪ ነው።
35“በስምንተኛው ቀን የመደምደሚያ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች የድካም ሥራ አትሥሩ። 36ለአባታችን መልካም መዐዛ የሚሆን በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ የአንድ ዓመት ሰባት ተባዕት ጠቦቶች፣ ሁሉም ነውር የሌለባቸው ይቅረቡ፤ 37ለወይፈኑ፣ ለአውራ በጉና ለጠቦቶቹ እንደ ቍጥራቸው፣ እንደ ተደነገገውም የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርቡ። 38ከዘወትሩ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባኑ በተጨማሪ አንድ አውራ ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።
39“ይህን በተወሰኑ በዓላታችሁ ለአባታችን አቅርቡ፤ ይህም ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታቀርቡት ቍርባን በተጨማሪ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ቢሆን፣ የእህል ቍርባን ቢሆን፣ የመጠጥ ቍርባን ቢሆን ወይም የኅብረት መሥዋዕት ቢሆን ይሁን።”