አስቀድመህ በራስህ ፍረድ
በሌላው ዓይን ያለውን ጉድፍ ከመንካትህ በፊት ከራስህ ዓይን ምሰሶውን አውጣ። ለምኑ፥ ይሰጣችኋል። አስተማሪዎችን በፍሬያቸው መዝኑ። ከዚያም ከባዱ መታጠፊያ፦ ‘ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ’ ማለትና ተአምራት እንኳ ማድረግ የአብን ፈቃድ ከማድረግ ጋር አንድ አይደለም።
7 1“እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ። 2በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል። 3በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ፤ በራስህ ዐይን ያለውን ምሰሶ ግን ለምን አትመለከትም? 4ወይስ በራስህ ዐይን ምሰሶ ሳለ፣ ወንድምህን፣ ‘ከዐይንህ ጉድፉን ላውጣ’ እንዴት ልትለው ትችላለህ? 5አንተ ግብዝ፣ አስቀድመህ ከራስህ ዐይን ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም የወንድምህን ዐይን ጉድፍ ለማውጣት በግልጽ ታያለህ።
6“የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቍዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ፤ በእግራቸው ይረግጧቸዋልና፤ ተመልሰውም ይነጣጥቋችኋል።
አባታችን ለሚለምኑት ይሰጣል
7“ለምኑ፤ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፤ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፤ ይከፈትላችኋል። 8የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። 9ወይስ ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማን ነው? 10ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋልን? 11እንግዲህ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፤ በሰማይ ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገሮችን አይሰጥም!
12“እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግና ነቢያት ይህ ነውና።
13“በጠበበው በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፤ በእርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው። 14ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
በፍሬያቸው ይታወቃሉ
15“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፤ የበግ ለምድ ለብሰው ይመጡባችኋል፤ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ናቸው። 16በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን? 17እንዲሁም መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ ክፉ ዛፍ ግን ክፉ ፍሬ ያፈራል። 18መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ ክፉ ዛፍም መልካም ፍሬ ማፍራት አይችልም። 19መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። 20እንግዲያስ በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።
የአባታችንን ፈቃድ የሚያደርጉ ብቻ
21“‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ የአባታችንን መንግሥት የሚገባ አይደለም፤ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ። 22በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል። 23በዚያን ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዐመፅ የምትሠሩ፣ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ።
በዐለት ላይ መሥራት
24“እንግዲህ እነዚህን ቃሎቼን ሰምቶ የሚያደርጋቸው ሁሉ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። 25ዝናብ ወረደ፤ ጎርፍ መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት መታው፤ ነገር ግን በዐለት ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። 26እነዚህን ቃሎቼን ሰምቶ የማያደርጋቸው ሁሉ ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሞኝ ሰውን ይመስላል። 27ዝናብ ወረደ፤ ጎርፍ መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ነበር።”
28ኢየሱስም ይህን ቃል ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ፣ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ፤ 29ትምህርቱ እንደ ጸሐፍቶቻቸው ሳይሆን፣ ሥልጣን እንዳለው ሆኖ ያስተምራቸው ነበርና።