በግርማ የተጐናጸፈ
ሁለት ነገሮች ሳይናወጡ ይቆማሉ፤ እነርሱም ዓለምና ዙፋኑ ናቸው። ጎርፎች ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፣ ማዕበላቸውንም ያጋጫሉ። መዝሙሩ ግን በአርያም ያለው አብ ከሞገዶቹ እጅግ እንደሚበረታ፣ ሥርዓቱም እንደ ንግሥናው የማይነቃነቅ እንደ ሆነ ይመልሳል።
93 1አባታችን ነግሦአል፤ ግርማን ተጐናጽፎአል። አባታችን ተጐናጽፎአል፤ ኀይልንም ታጥቆአል። በርግጥም ዓለም ጸንታ ተመሥርታለች፤ ከቶ አይነቃነቅም። 2ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ ጸንቶ ቆሟል፤ አንተ ከዘላለም ነህ። 3አባታችን ሆይ፣ ወንዞች ከፍ ብለዋል፤ ወንዞች ድምፃቸውን ከፍ አድርገዋል፤ ወንዞች ነዋጭ ማዕበላቸውን ከፍ አድርገዋል። 4ከብዙ ውሃዎች ድምፅ ይልቅ፣ ከባሕር ማዕበል ይልቅ፣ በላይ ያለው አባታችን ኀያል ነው። 5ምስክሮችህ እጅግ የታመኑ ናቸው፤ አባታችን ሆይ፣ ቅድስና ለቤትህ ለዘላለም ይገባል።