ማኅተማቸውን ያተሙት
በታተመ ሰነድ ላይ ያሉ ስሞች፤ ካህናት፣ ሌዋውያንና የቤተ ሰብ አለቆች ለተወሰኑ ነገሮች ራሳቸውን በመሐላ ለአብ ያስራሉ፤ ከአካባቢው ሕዝቦች ጋር ጋብቻ እንዳይኖር፣ በሰንበት እንዳይገዛ፣ በየሰባተኛው ዓመት ዕዳ እንዲተው፣ ለቤተ መቅደሱ ሥራና ለሠራተኞቹም የማያቋርጥ ድጋፍ እንዲሰጥ።
10 1ማኅተማቸውን ያተሙትም እነዚህ ነበሩ፦ የሐካልያ ልጅ ገዥው ነህምያ፣ ሴዴቅያስ፣ 2ሠራያ፣ አዛርያ፣ ኤርምያስ፣ 3ጳስኆር፣ አማርያ፣ መልክያ፣ 4ሐጡስ፣ ሸባንያ፣ ማሉክ፣ 5ሐሪም፣ ሜሬሞት፣ አብድዩ፣ 6ዳንኤል፣ ጊኔቶን፣ ባሮክ፣ 7መሱላም፣ አብያ፣ ሚያሚን፣ 8መዓዝያ፣ ቢልጋይ፣ ሸማያ። እነዚህ ካህናቱ ነበሩ። 9ሌዋውያኑም፦ የአዛንያ ልጅ ኢያሱ፣ ከሔናዳድ ልጆች የሆነው ቢኑሂ፣ ቃድሚኤል፣ 10ባልንጀሮቻቸው ሌዋውያኑም፦ ሸባንያ፣ ሆድያ፣ ቀሊጣ፣ ፈላያ፣ ሃናን፣ 11ሚካ፣ ረኆብ፣ ሐሻብያ፣ 12ዛኩር፣ ሰራብያ፣ ሸባንያ፣ 13ሆድያ፣ ባኒ፣ ቤኒኑ። 14የሕዝቡ መሪዎች፦ ፋሮስ፣ ፈሐት ሞዓብ፣ ኤላም፣ ዛቱ፣ ባኒ፣ 15ቡኒ፣ አዝጋድ፣ ቤባይ፣ 16አዶንያ፣ ቢግዋይ፣ ዓዲን፣ 17አጤር፣ ሕዝቅያስ፣ አዙር፣ 18ሆድያ፣ ሐሱም፣ ቤሳይ፣ 19ሐሪፍ፣ ዓናቶት፣ ኔባይ፣ 20መግፊዓስ፣ መሱላም፣ ሔዚር፣ 21መሼዛብኤል፣ ሳዶቅ፣ ያዱዓ፣ 22ፈላጥያ፣ ሃናን፣ ዓናያ፣ 23ሆሴዕ፣ ሐናንያ፣ ሐሱብ፣ 24ሃሎሔስ፣ ፒልሃ፣ ሾቤቅ፣ 25ረኁም፣ ሐሻብና፣ መዓሴያ፣ 26አኪያ፣ ሃናን፣ ዓናን፣ 27ማሉክ፣ ሐሪም፣ በዓና።
ሕዝቡ ራሳቸውን ለአባታችን አሰሩ
28የተቀሩት ሕዝብም፦ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ በረኞቹ፣ ዘማሪዎቹ፣ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና ስለ አባታችን ሕግ ራሳቸውን ከአገሮቹ ሕዝቦች የለዩ ሁሉ፣ ከሚስቶቻቸው፣ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆቻቸው ጋር፣ ዕውቀትና ማስተዋል ያላቸው ሁሉ፣ 29እነዚህ ሁሉ ከወንድሞቻቸው ከመኳንንቱ ጋር ተባበሩ፤ በአገልጋዩ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የአባታችንን ሕግ ለመከተል፣ የጌታ አባታችንንም ትእዛዛት ሁሉ፣ ፍርዱንና ሥርዐቱን ለመጠበቅና ለመፈጸም በእርግማንና በመሐላ ራሳቸውን አሰሩ። 30ሴቶች ልጆቻችንን በዙሪያችን ላሉት ሕዝቦች በጋብቻ ላለመስጠት፣ የእነርሱንም ሴቶች ልጆች ለወንዶች ልጆቻችን ላለማጋባት ቃል እንገባለን። 31የአገሩ ሕዝቦች በሰንበት ቀን የሚሸጡትን ሸቀጥ ወይም እህል ቢያመጡ፣ በሰንበት ቀን ወይም በማንኛውም ቅዱስ ቀን ከእነርሱ አንገዛም። በየሰባተኛውም ዓመት መሬቱ እንዲያርፍ እናደርጋለን፤ ዕዳንም ሁሉ እንሰርዛለን።
32ደግሞም ለአባታችን ቤት አገልግሎት በየዓመቱ የአውንስ አንድ ስምንተኛ ብር ለመስጠት ራሳችንን እናስራለን፦ 33በፊቱ ለሚቀርበው ኅብስት፣ ለዘውትር የእህልና የሚቃጠል መሥዋዕት፣ ለሰንበት፣ ለመባቻና ለበዓል መሥዋዕቶች፣ ለቅዱሳን ስጦታዎች፣ እስራኤልንም ለማስተሥረይ ለኀጢአት መሥዋዕቶች፣ ለአባታችን ቤት ሥራ ሁሉ ይሆናል። 34እኛም ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና ሕዝቡ በሕጉ እንደ ተጻፈ፣ በአባታችን መሠዊያ ላይ ለማቃጠል በየዓመቱ በተወሰነ ጊዜ እንደ ቤተ ሰባችን ወደ አባታችን ቤት ለማምጣት ስለ እንጨቱ መባ ዕጣ ተጣጣልን። 35ደግሞም የመሬታችንን በኵራትና የማንኛውንም ዛፍ ፍሬ በኵራት ዓመት በዓመት ወደ አባታችን ቤት ለማምጣት ራሳችንን ግዴታ እናደርጋለን። 36እንዲሁም በሕጉ እንደ ተጻፈ የወንዶች ልጆቻችንንና የከብቶቻችንን በኵራት፣ የላሞቻችንንም ሆነ የበጎቻችንን በኵራት ወደ አባታችን ቤት፣ በዚያ ወደሚያገለግሉት ካህናት እናመጣለን። 37የመጀመሪያውን ቂጣችንን፣ መባዎቻችንን፣ የማንኛውንም ዛፍ ፍሬ፣ አዲሱን የወይን ጠጅና ዘይት ወደ ካህናቱ፣ ወደ አባታችን ቤት ጎተራዎች እናመጣለን፤ የመሬታችንንም ዐሥራት ወደ ሌዋውያኑ እናመጣለን፤ ምክንያቱም ሌዋውያኑ በሚያርሱ ከተሞቻችን ሁሉ ዐሥራቱን ይሰበስባሉና። 38ሌዋውያኑ ዐሥራቱን በሚሰበስቡበት ጊዜ ከአሮን ዘር የሆነ ካህን ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ ሌዋውያኑም ከዐሥራቱ ዐሥራት አውጥተው ወደ አባታችን ቤት፣ ወደ ግምጃ ቤቱ ጎተራዎች ያወጣሉ። 39የእስራኤል ሕዝብና ሌዋውያኑ የእህሉን፣ አዲሱን የወይን ጠጅና የዘይቱን መባ የመቅደሱ ዕቃዎች ወዳሉበት ጎተራዎች፣ የሚያገለግሉት ካህናት፣ በረኞችና ዘማሪዎች ወዳሉበት ያመጣሉ። የአባታችንንም ቤት ቸል አንልም።